በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ፣ በነጭ ሣር ብሄራዊ ፓርክና በGIZ ትብብር በጫሞ ሐይቅ ላይ ለዓሳ መራቢያነት በተከለለው 100 ሄክታር የመራቢያ ቦታ ምክንያት በሐይቁ ላይ ጠፍተው የነበሩ እንደ <<Labeobarbus bynni>> እና ከዚህ ቀደም ታይተው የማይታወቁ <<Shilbe intermedius>> የተሰኙ ሁለት የዓሳ ዝርያዎች መገኘታቸው ተገልጿል፡፡  ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ   

የAMU-IUC ፕሮግራም ኃላፊና የዘርፉ ተመራማሪ ዶ/ር ፋሲል እሸቱ እንደገለጹት ጫሞ ሐይቅ ሊሸከም ከሚችለው በላይ አስጋሪዎች ዓሳ የማስገር ተግባር ስለሚያከናውኑበት የሐይቁ የዓሳ ምርት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተመናመነ እንዲመጣ ካደረጉ ምክንያቶች መካከል አንዱ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ በመሆኑም ለዓሳ መራቢያ የሚሆን ቦታ ከልሎ አስፈላጊውን ጥበቃና ክትትል ማድረግ አስፈላጊና ወሳኝ ሆኖ በመገኘቱ ሁሉንም ባለድርሻ አካላት በማሳተፍ ምቹ ቦታ ተመርጦ 100 ሄክታር የሚሆን የሐይቁን ከፍል መከለል መቻሉን ተመራማሪው ተናግረዋል፡፡ ለመራቢያነት በተከለለውና ከሰው ንኪኪ ከ2 ዓመታት በላይ ነፃ እንዲሆን በተደረገው የሐይቁ ክፍል የዓሳ ምርት እየጨመረ በመምጣቱ ከዚህ ቀደም ከሐይቁ ላይ ጠፍተውና ታይተው የማይታወቁ ዝርያዎች መገኘታቸውን ዶ/ር ፋሲል ተናግረዋል፡፡

አሁን ላይ በሐይቁ ከዓሳ ምርታማነት መጨመር ጋር ተያይዞ እየታየ ያለውን ለውጥና ውጤት ለማስቀጠል በሐይቁ የተለያዩ አቅጣጫዎች 4 ተጨማሪ የዓሳ መራቢያ ቦታዎችን ለማዘጋጀት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየተሠራ ሲሆን ይህም በቅርቡ እውን እንደሚሆን ተመራማሪው ገልጸዋል፡፡

በጫሞ ሐይቅ ላይ ከተሠማሩ አስጋሪዎች አንዱ የሆኑት አቶ ሀብታሙ ጌታሁን እንደገለጹት አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የመራቢያ ሥፍራውን ከከለለ ወዲህ የሚያገኙት የዓሳ ምርት በፊት ከነበረው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱን ተናግረዋል፡፡ ከዚህም ባሻገር ከዚህ ቀደም ታይተው የማይታወቁ አዲስ ዝርያዎችም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየታዩ ነው ብለዋል፡፡ ለዓሳ ዝርያዎቹ መራቢያ የሚሆን ስፍራ በሐይቁ ላይ ከልሎ ማስቀመጥ አስፈላጊ መሆኑን በመገንዘብ በራሳቸው አቅም ተጨማሪ የመራቢያ ሥፍራዎችን ከልሎ ለማስቀመጥ ጥረት እያደረጉ መሆኑንም አቶ ሀብታሙ ጠቁመዋል፡፡

በሐይቁ ላይ የዓሳ ምርት እየጨመረ መሆኑና የጠፉ ዝርያዎች ዳግም መታየት መጀመራቸው በአጭር ጊዜ ውስጥ የታየ አበረታች ለውጥ በመሆኑ ይህም በትብብር መሥራት ከተቻለ የተፈጥሮ ሀብቶቻችንን መጠበቅና ወደ ነበሩበት መመለስ እንደሚቻል አመላካች ነው፡፡ ስለሆነም እየታየ ያለው ጅምር ውጤት ተጠናክሮ እንዲቀጥልና ሌሎች ተጨማሪ ተግባራትን ለማከናወን ሁሉም ባለድርሻ አካላት በትብብር ሊሰሩ ይገባል፡፡

 

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት