ዩኒቨርሲቲው በተለያዩ የትምህርት መስኮች በመጀመሪያ፣ በ2ኛና በ3ኛ ዲግሪ ፕሮግራሞች ያሠለጠናቸውን 6,730 ተማሪዎች ለ34ኛ ጊዜ መስከረም 29/2014 ዓ/ም አስመርቋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ የፕሮፌሰርነት አካዳሚክ ማዕረግ ለአንድ መምህርና ተመራማሪም ሰጥቷል። ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ   

በቅድመ ምረቃ ወንድ 3,910 ሴት 2,124 በድምሩ 6,034፣ በድኅረ-ምረቃ 2ኛ ዲግሪ ወንድ 463 ሴት 54 እና በ3ኛ ዲግሪ ወንድ 5 በድምሩ 522 በሁሉም ፕሮግራሞች ወንድ 4,518 ሴት 2,212 በአጠቃላይ 6,730 ተማሪዎች የሚፈለግባቸውን የመመረቂያ መስፈርት ማሟላታቸውን በማረጋገጥ የዩኒቨርሲቲው ሴኔት መስከረም 27/2014 ዓ.ም ባደረገው ጠቅላላ ጉባዔ ማጽደቁን የዩኒቨርሲቲው ሬጂስትራርና አልሙናይ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ማሌቦ ማንቻ ገልጸዋል፡፡

በምረቃ መርሃ-ግብሩ ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተርና የዩኒቨርሲቲው አስተዳደር ቦርድ ሰብሳቢ ዶ/ር ሹመቴ ግዛው ዩኒቨርሲቲዎች በምርምርና ቴክኖሎጂ ዘርፍ የሚያከናውኑትን ሥራ ማጠናከር እንደሚገባቸው ተናግረዋል፡፡ ለተመራቂዎች ባስተላለፉት መልዕክት የሀገራችን ችግሮች መፍቻ ቁልፉ ትምህርት እንደመሆኑ ምሩቃን ሕዝባችሁንና ሀገራችሁን ለማገልገል መዘጋጀት አለባችሁ ብለዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ ዩኒቨርሲቲው የ2013 ዓ/ም ተመራቂዎችን ጨምሮ ባለፉት 34 ዓመታት ከ69,000 በላይ ተማሪዎችን በማስመረቅ ለሀገሪቱ የሠለጠነ የሰው ኃይል ማፍራት መቻሉን አውስተው በተለይም በውሃ ምኅንድስና ዘርፍ ሀገራቸውን በተለያዩ የውሃ ፕሮጀክት ሥራዎች የሚያገለግሉ ባለሙያዎችን ማብቃት ተችሏል ብለዋል።

ተመራቂ ተማሪዎች በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው የተላበሱትን መልካም ስብዕና በማስቀጠል በሚሰማሩበት የሀገራችን አካባቢዎች ሁሉ ባካበቱት ዕውቀትና ክሂሎት በቅንነት ማገልገል እና ለሰላምና አንድነት ቅድሚያ መስጠት እንዳለባቸው ዶ/ር ዳምጠው አሳስበዋል፡፡

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ አልሙናይ ማኅበር ጸሐፊ ወ/ሮ ሣልሳዊት ባይነሳኝ ተመራቂዎች ሀገራችን በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ብትሆንም በትዕግስትና ተስፋ ባለመቁረጥ ለምረቃ በመብቃታችሁ እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል፡፡ አልሙናይ ማኅበሩ ባለፉት 3 ዓመታት ለዩኒቨርሲቲውና ለአካባቢው ማኅበረሰብ በበጎ አድራጎት፣ በመማር ማስተማርና ሥራ በማፈላለግ የተለያዩ ተግባራትን ማከናወኑን ገልጸው ወደ ፊትም ይህንኑ ሥራ ከዩኒቨርሲቲው ጋር በመተባበር አጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል፡፡

በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ ከየትምህርት ክፍላቸው የላቀ ውጤት ላስመዘገቡ ተመራቂዎች የሜዳሊያ ሽልማት እዲሁም ከሴቶች ከፍተኛ ውጤት ላመጡ ተመራቂዎች ልዩ ሽልማት ተበርክቷል፡፡

ዩኒቨርሲቲው በግብርና ሳይንስ ኮሌጅ በመምህርነትና በተመራማሪነት እያገለገሉ ለቆዩት ለዶ/ር ይስሐቅ ከቸሮ የሙሉ ፕሮፌሰርነት አካዳሚክ ማዕረግ በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ ሰጥቷል።

     

     የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት