Print

በዩኒቨርሲቲው 6ኛው ዙር ዓመታዊ የማኅበረሰብ ሳምንት ‹‹በተፈጠረው እድል ማኅበረሰባችንን እናገልግል›› በሚል መሪ ቃል መስከረም 28/2014 ዓ/ም በደማቅ ሁኔታ ተከብሯል፡፡ 

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ በመክፈቻ ንግግራቸው ዩኒቨርሲቲው ለሀገሪቱ እድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ የሚያበረክቱ ባለሙያዎችን ከማፍራት ጎን ለጎን ሰፊ የማኅበረሰብ አገልግሎት ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው የማኅበረሰብ አገልግሎት ዘርፍ መዋቅሩን በሰው ኃይልና በግብዓት በማጠናከር፣ ፈጠራንና የቴክኖሎጂ ሸግግርን በማስፋፋት የተሻለ አገልግሎት ለማኅበረሰቡ ለመስጠት ስትራቴጂክ ዓላማ አስቀምጦ እየሠራ እንደሚገኝ ፕሬዝደንቱ ተናግረዋል፡፡ የማኅበረሰብ ሳምንት በየዓመቱ መከበሩ እንደ ባህል እያደገ የመጣ ሲሆን ለወደፊቱም የተሻሉ አፈጻጸሞችን በማከል ተጠናክሮ የሚቀጥል ተግባር ይሆናልም ብለዋል፡፡  ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የዩኒቨርሲቲው የማኅበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ተክሉ ወጋየሁ በበኩላቸው የማኅበረሰብ ሳምንት መከበሩ የተከናወኑ ሥራዎችን ለማኅበረሰቡ ለማሳወቅ እንዲሁም በአፈጻጸም ሂደቱ ላይ ሃሳብና አስተያየቶችን ለመቀበል እንደሚረዳ ተናግረዋል፡፡

ዶ/ር ተክሉ በጉባዔው ባቀረቡት የሥራ ክንውን ሪፖርት እንደገለጹት በበጀት ዓመቱ በምርምርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ፕሮጀክት ቀርከሃን ማልማትና መጠቀም፣ ሽመናን ማዘመንና የገበያ ትስስር መፍጠር፣ የሳሙናና ሳኒታይዘር ምርት ማዘጋጀትና ማሰራጨት ተሠርተዋል፡፡ ከዚህም ባሻገር የተቀናጀ የአካባቢ ጥበቃና ተፋሰስ ልማት፣ የአረንጓዴ አሻራ ልማት፣ ተግባር ተኮር የጎልማሶች ትምህርትና ሥልጠና፣ አቅም ለሌላቸው አረጋውያንና ሕፃናት ነፃ የሕግ ድጋፍ አገልግሎት፣ ማዕድ ማጋራትና የአልባሳት ድጋፍ፣ ለወላጅ አጥ ሕፃናት የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ፣ በወጣቶች ላይ የሥነ-ምግባር ግንባታ ሥራዎች፣ በተፈጥሮም ሆነ በሰው ሠራሽ ምክንያቶች ለተፈናቀሉ ዜጎች ድጋፍ እንዲሁም የደም ልገሳ በዩኒቨርሲቲው የማኅበረሰብ አገልግሎት ዘርፍ የተከናወኑ ተግባራት ናቸው፡፡

የጋሞ ዞን ዋና አስተዳዳሪና የዩኒቨርሲቲው ም/ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ብርሃኑ ዘውዴ በዩኒቨርሲቲው የማኅበረሰብ ሳምንት መከበሩ ለኅብረተሰቡ የተሰጡ አገልግሎቶችን በተግባር የምናይበት፣ በሚሠሩ ሥራዎች ላይ ጊዜ ሰጥተን እንድንወያይ የሚረዳ ብሎም ከዩኒቨርሲቲው ጋር ያለንን ቀረቤታ የሚያጠናክርልን ነው ብለዋል፡፡ በቀጣይም ከዩኒቨርሲቲው ጎን በመቆም ከኅብረተሰቡ ለሚነሱ ጥያቄዎች በጋራ መልስ ለመስጠት እንሠራለንም ብለዋል፡፡

በዕለቱ ዩኒቨርሲቲው በተግባር ተኮር የጎልማሶች ትምህርት ዘርፍ ለተከታታይ ሁለት ዓመታት ያስተማራቸውን 340 ተማሪዎች ያስመረቀ ሲሆን ዩኒቨርሲቲው በ1 ሚሊየን ብር ወጪ ያሠራው ከአርባ ምንጭ ሻራ ቀበሌ እስከ አቡሎ ንዑስ መንደር 3.5 ኪሜ የጠጠር መንገድ የምረቃ ሥነ-ሥርዓት ተካሂዷል፡፡ በተጨማሪም ለ 2 ት/ቤቶች የመማሪያ መጽሐፍ ድጋፍና የተለያዩ ዓውደ ርይዮችም ተካሂደዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራሮችና መምህራን፣ የተለያዩ መሥሪያ ቤቶች የሥራ ኃላፊዎች፣ የሃይማኖት አባቶች እንዲሁም የጋሞ አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች በጉባዔው ተገኝተዋል፡፡

 

     የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት