Print

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ሳውላ ካምፓስ በተለያዩ የትምህርት መስኮች ያሠለጠናቸውን በድኅረ ምረቃ 7 እና በቅድመ ምረቃ 674 በአጠቃላይ 681 ተማሪዎች መስከረም 30/2014 ዓ/ም አስመርቋል፡፡ ከተመራቂዎቹ መካከል 252ቱ ሴቶች ናቸው፡፡  ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ      

የዕለቱ የክብር እንግዳ የጎፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪና የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የቦርድ አባል ዶ/ር ጌትነት በጋሻው ለተመራቂዎች ባስተላለፉት መልዕክት ሀገራችን ኢትዮጵያ የፀጥታ ችግሮችና የኮቪድ ወረርሽን ስጋት በተጋረጡባት ወቅት አስቸጋሪ ጊዜያትን በጽናት አልፋችሁ ለምረቃ ዕለት በመድረሳችሁ እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል፡፡

ተመራቂዎች የጎጠኛና ከፋፋይ ኃይሎች ትርክት ሰለባ ሳይሆኑ ለሀገር አንድነትና ልማት በጋራ እንዲቆሙ እንዲሁም በየዕውቀት ዘርፋቸው ሀገራቸውን በቀናነት እንዲያገለግሉ ዶ/ር ጌትነት አሳስበዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ የተፈጥሮ ሀብትና የብዝሃ ባህል ባለቤት የሆነችውን ሀገራችን ኢትዮጵያ እድገትና ክብር ከፍ ለማድረግ ሀብቷን በአግባቡ መጠቀምና ሰላሟን ማስከበር እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡ ለዚህም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትና ምሩቃን ሚና ከፍተኛ እንደመሆኑ አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲም የበኩሉን ድርሻ በመወጣት ላይ የሚገኝ መሆኑን ገልጸው ምሩቃን ላስተማረቻችሁ ሀገር እድገት፣ ሰላምና አንድነት የተቻላችሁን ሁሉ ማበርከት ይጠበቅባችኋል ብለዋል፡፡

በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ ከካምፓሱ ከፍተኛ ውጤት ላስመዘገቡ ተማሪዎች የወርቅ ሜዳሊያ እና ከሴቶች የላቀ ውጤት ላመጡ ልዩ ሽልማት ተበርክቷል፡፡

ሳውላ ካምፓስ በ2008 ዓ/ም በ4 የትምህርት ፕሮግራሞች 191 ተማሪዎችን ተቀብሎ ማስተማር የጀመረ ሲሆን በአሁኑ ጊዜ 2,440 ተማሪዎችን በማስተማር ላይ ይገኛል፡፡ የ2013 ዓ/ም ተመራቂዎችን ጨምሮ ካምፓሱ እስከ አሁን 1,299 ተማሪዎችን ለምረቃ አብቅቷል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት