አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በዩኒቨርሲቲው የ34 ዓመታት ታሪክ የመጀመሪያውን የሙሉ ፕሮፌሰርነት ማዕረግ በግብርና ሳይንስ ኮሌጅ የእንስሳት ሳይንስ መምህርና ተመራማሪ ለሆኑት ለዶ/ር ይስሃቅ ከቸሮ ከበደ ሰጥቷል፡፡



ፕ/ር ይስሃቅ ከቸሮ በጋሞ ዞን ቦንኬ ወረዳ ካቻ ሠንጋ ቀበሌ በ1970 ዓ/ም የተወለዱ ሲሆን የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን በካቻ ሲንጋ 1ኛ ደረጃ ት/ቤትና አርባ ምንጭ ከተማ በሚገኘው ኩልፎ መለስተኛ 2ኛ ደረጃ ት/ቤት እና የ2ኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በአርባ ምንጭ አጠቃላይ 2ኛ ደረጃ ት/ቤት ተከታትለዋል፡፡

የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በ1992 ዓ/ም እና 2ኛ ዲግሪያቸውን በ1997 ዓ/ም ከሐሮማያ ዩኒቨርሲቲ በእንስሳት ሳይንስ የትምህርት መስክ አግኝተዋል፡፡ ፕሮፌሰሩ የምርምር ሥራቸውን ‹‹Animal Nutrition and Feed Evaluation Models for Economically Important Animals›› በሚል ርዕስ በማከናወን በ‹‹Animal Nutrition and Feed Technology (Veterinary Science) ትምህርት መስክ በ2005 ዓ/ም ቤልጂየም ሀገር ከሚገኘው ግሄንት ዩኒቨርሲቲ ‹‹Ghent University›› 3ኛ ዲግሪያቸውን ማግኘት ችለዋል፡፡

ከ1993 ዓ/ም - 1997 ዓ/ም በካምባ ወረዳ የ‹‹Integrated Rural Development Project EKHC›› ፕሮጀክት ማኔጀር በመሆን እንዲሁም የቦንኬ ወረዳ ግብርናና የገጠር ልማት ኃላፊ በመሆን የሠሩት ፕሮፌሰሩ በ1997 ዓ/ም አንጋፋውን የጂማ ዩኒቨርሲቲ ግብርናና እንስሳት ሕክምና ኮሌጅ ተቀላቅለዋል፡፡

ባከናወኗቸው በርካታ የምርምርና ማኅበረሰብ አገልግሎት ሥራዎች ከጂማ ዩኒቨርሲቲ በ2003 ዓ/ም የተባባሪ ፕሮፌሰርነት ማዕረግ ያገኙት ዶ/ር ይስሃቅ ከ60 በላይ ‹‹Peer Reviewed›› የምርምር ጆርናሎችን ማሳተም የቻሉ ሲሆን ከምርምሮቹ የ32ቱ ዋና ተመራማሪ (Principal Investigator) በመሆን ሠርተዋል፡፡ በተጨማሪም በተለያዩ የምርምር መጽሔቶች ላይ 14 አርቲክሎችን ያሳተሙ ሲሆን 30 የምርምር ውጤቶቻቸውን በተለያዩ ሀገር አቀፍና ዓለም ዓቀፍ የምርምር መድረኮች ላይ ማቅረብ ችለዋል፡፡

ፕ/ር ይስሃቅ ቤልጂየምና ኔዘርላንድ ሀገር በሚገኙ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት 47 የ2ኛ ዲግሪ የምርምር ሥራዎች ላይ ሱፐርቫይዘር በመሆን እንዲሁም 53 የ2ኛና የ3ኛ ዲግሪ የመመረቂያ ጽሑፎች ገምጋሚ በመሆን በርካታ ተማሪዎችን ማስመረቅም ችለዋል፡፡ ባከናወኗቸው በርካታ የምርምርና የማኅበረሰብ አገልግሎት ሥራዎች ቤልጂየም ሀገር ከሚገኘው ግሄንት ዩኒቨርሲቲ ከእንስሳት ሕክምና ፋከልቲ ዕውቅናና ሽልማት አግኝተዋል፡፡

በ2007 ዓ/ም የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ግብርና ሳይንስ ኮሌጅን የተቀላቀሉት ፕ/ር ይስሃቅ በእስካሁን የዩኒቨርሲቲው ቆይታቸው ለ3 ዓመታት የግብርና ኮሌጅ ዲን፣ በAMU-IUC ፕሮግራም የ ‹‹Improving Agricultural Productivity in the South Ethiopian Rift Valley›› ፕሮጀክት ኃላፊ፣ ‹‹International Food Security Research and Development Program/Orange Knowledge Program/ called MSM-BFA-South” ፕሮጀክት አስተባባሪ፣ የ‹‹OMO International Journal of Sciences›› ዋና አርታኢ፣ የ‹‹International Journal of Animal Science and Livestock Production›› ተባባሪ አርታኢ፣ የ ‹‹International Journal of Veterinary Science and Research›› ተባባሪ አርታኢ፣ በአርባ ምንጭ

ዩኒቨርሲቲ የ ‹‹Research and Development Standing Committee›› አባል እንዲሁም በዩኒቨርሲቲው በሚሠሩ የተለያዩ ሜጋ ፕሮጀክቶች ዋና ተመራማሪ/Principal Investigator/ በመሆን ዩኒቨርሲቲውንና ማኅበረሰቡን አገልግለዋል፤ እያገለገሉም ይገኛሉ፡፡

ከዚህም በተጨማሪ ፕሮፌሰሩ በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው 2 የ3ኛ ዲግሪና 4 የ2ኛ ዲግሪ የትምህርት ፕሮግራሞችን አዘጋጅተው እንዲከፈቱ በማድረግ በዩኒቨርሲቲው የድኅረ-ምረቃ ፕሮግራሞች መስፋፋት እንዲሁም የእንስሳትና ዓሳ ሀብት ልማት ምርምር ማዕከል በማቋቋም ሂደትም የበኩላቸውን የላቀ አስተዋጽኦ አበርክተዋል፡፡

ፕ/ር ይስሃቅ ከቸሮ ሙሉ ፕሮፌሰር መሆናቸውን አስመልክቶ በሰጡት አስተያየት በተለይ በዩኒቨርሲቲው ታሪክ የመጀመሪያው ሙሉ ፕሮፌሰር መሆን በመቻላቸው ትልቅ ደስታ እንደተሰማቸው ገልጸው በቀጣይም የማኅበረሰቡን ችግር የሚፈቱ ምርምሮችን ማከናወን ላይ ትኩረት እንደሚያደርጉ ተናግረዋል፡፡ 80 በመቶ የሚሆነው የሀገራችን ሕዝብ አርሶና አርብቶ አደር መሆኑን የጠቆሙት ፕ/ር ይስሃቅ የአርሶና አርብቶ አደሩን ሕይወት መቀየር የሚያስችሉ አዳዲሰና ዘመናዊ አሠራሮችን ለማበልጸግና የግል ልምድና ተሞክሯቸውን ለሌሎች ለማካፈል ትኩረት ሰጥተው እንደሚሠሩ ጠቁመዋል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲና የዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ ፕ/ር ይስሃቅ ከቸሮ በዩኒቨርሲቲው ታሪክ የመጀመሪያው ሙሉ ፕሮፌሰር በመሆንዎ እንኳን ደስ አልዎት እያለ ቀጣይ የሥራ ዘመንዎ የስኬት እንዲሆንልዎት መልካም ምኞቱን ይገልጻል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት