የቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ ከቱሪዝምና ሆቴል ማኔጅመንት ት/ክፍል ጋር በመተባበር በቱሪዝምና ሆስፒታሊቲ ማኔጅመንት የ2ኛ ዲግሪ ትምህርት ለመክፈት የሚያስችል የውጭ ሥርዓተ-ትምህርት ግምገማ መስከረም 20/2014 ዓ/ም አካሂዷል፡፡  ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ   

የአካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር ዓለማየሁ ጩፋሞ እንደገለጹት አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የምርምር ዩኒቨርሲቲ እንደመሆኑ የተለያዩ ምርምር ተኮር የድኅረ ምረቃ ፕሮግራሞችን ማመቻቸት ይጠበቅበታል፡፡ ዩኒቨርሲቲዎች ጥራቱን የጠበቀና ሀገራዊ ፍላጎትን ከግንዛቤ ያስገባ ፕሮግራም በመቅረጽ ብቁና ተወዳዳሪ የሰው ኃይል በማፍራት ላይ ትኩረት እንዲያደርጉ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ማሳሰቡን ዶ/ር ዓለማየሁ ተናግረዋል፡፡ በዚህም መሠረት የቢዝነስና ኦኮኖሚክስ ኮሌጅ የሚያስጀምረው ፕሮግራም ጥራቱን የጠበቀ እንዲሆን ዩኒቨርሲቲው አስፈላጊውን የሰው ኃይልና ቁሳቁስ በማሟላት ኃላፊነቱን ይወጣል ብለዋል፡፡

የቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ ዲን ዶ/ር መስፍን መንዛ በቱሪዝምና ሆስፒታሊቲ ማኔጅመንት የ2ኛ ዲግሪ ትምህርት ለመክፈት ከዚህ በፊት የውስጥ ግምገማ መደረጉን አስታውሰው ከውስጥና ከውጭ ግምገማው የተገኙ አስተያየቶችን በማካተት ደረጃውን የጠበቀ ሥርዓተ-ትምህርት የሚዘጋጅ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ጭስ አልባ ኢንደስትሪ በመባል የሚታወቀው ቱሪዝም የሀገሪቷን እድገትና ልማት ሊያፋጥን የሚችል እምቅ ሀብት የያዘ ዘርፍ በመሆኑ እንደ ሀገር ትልቅ ትኩረት የተሰጠው መሆኑን ዶ/ር መስፍን ገልጸዋል፡፡ በመስኩ የትምህርት ፕሮግራም መከፈቱ አካባቢው የቱሪስት መዳረሻ በመሆኑ ያልተጠኑ ባህላዊ እሴቶችን ለማስተዋወቅና ከተለያዩ ኢንደስትሪዎች ጋር ትስስር በመፍጠር አካባቢውን ብሎም ሀገሪቱን ተጠቃሚ ለማድረግ እንደሚያስችል ተናግረዋል፡፡

የቱሪዝምና ሆቴል ማኔጅመንት መምህር ዶ/ር አሰግድ አየለ እንደገለጹት ቱሪዝም ለሀገር እድገት ቁልፍ በመሆኑ ሥርዓተ- ትምህርት ሲቀረጽ የተለያዩ የሀገር ውስጥ ዩኒቨርሲቲዎች ልምድ፣ የገበያውና የተማሪን ፍላጎት እንዲሁም ዲጂታል ኢኮኖሚው ጋር ያለውን ቁርኝት የዳሰሳ ጥናት መደረጉን ጠቁመዋል፡፡ ዶ/ር አሰግድ በትምህርት መርሃ ግብሩ እንደ ሀገር ያለው ባለሙያ ውስን በመሆኑ መርሃ-ግብሩ መከፈቱ የባለሙያ እጥረትን የሚቀንስና ፋይዳው የጎላ ነው ብለዋል፡፡

በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የቱሪዝምና ሆስፒታሊቲ ማኔጅመንት መምህር ረ/ፕ አማረ ያዕቆብ እንደ ውጭ ገምጋሚ ሥርዓተ- ትምህርቱን የበለጠ ሊያዳብሩ የሚችሉ በየትምህርት ዓይነቱና በይዘቱ ላይ መካተት ያለባቸውን በማመላከት የራሳችንን ሙያዊ ምልከታ ሰጥተናል ብለዋል

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት