የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ሥራ ፈጠራ ልማት ማፍለቂያ ማዕከል በሁሉም ካምፓሶች ለሚገኙ የ2014 ዓ/ም ዕጩ ተመራቂ ተማሪዎች ከመስከረም 25-26/2014 ዓ/ም የሥራ ፈጠራ ክሂሎት /Entrepreneurship Skill/ ሥልጠና ሰጥቷል፡፡ 

በሥልጠናው እንደተገለጸው በሀገሪቱ በየጊዜው የሚመረቁ ተማሪዎች ቁጥር እጅግ ከፍተኛ ሲሆን የመንግሥትም ሆነ የግል ተቋማት የቅጥር አቅም ተመጣጣኝ አይደለም፡፡ በመሆኑም ተማሪዎች ከዩኒቨርሲቲ ተመርቀው ሲወጡ ሥራ ፈላጊ ከመሆን ይልቅ በአካባቢያቸው ያሉ ችግሮችን ወደ መልካም አጋጣሚ በመቀየር ሥራ ፈጣሪ እንዲሆኑ ለማስቻል ሥልጠናው ተዘጋጅቷል፡፡     ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

በተጨማሪም ሥልጠናውን መውሰዳቸው የቢዝነስ ሃሳባቸውን በተደራጀ መልኩ በጽሑፍ ይዘው ከተለያዩ የፋይናንስ ድርጅቶች ጋር ትስስር በመፍጠር ከተመረቁበት የትምህርት መስክ ባሻገር ሰፊ የሥራ ፈጠራ ክሂሎት እንዲኖራቸው ይረዳል፡፡

በሥልጠናው መሠረታዊ የሥራ ፈጠራ ክሂሎትን ማሳደግና አመለካከትን መቀየር፣ በገበያ ላይ ተወዳዳሪና ብቁ ለመሆን የሚጠበቁ ነጥቦች እንዲሁም የቢዝነስ ዕቅድ አዘገጃጀት ርዕሰ ጉዳዮች በስፋት ተዳሰዋል፡፡

ሠልጣኝ ተማሪዎች የሥራ ፈጠራ ልምዳችንን በማጎልበት ከመንግሥት ሥራን ጠባቂ ከመሆን ይልቅ በቀላሉ ወደ ሥራ ዓለም በመግባት ውጤታማና ትርፋማ እንድንሆን የሚያግዝ ክሂሎት አግኝተናል ብለዋል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት