Print

በኢ.ፌ.ዴ.ሪ. የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር የከፍተኛ አመራር ዝግጅት ምልመላና ስምሪት ሥርዓት ማስተባበሪያ መመሪያ መሠረት ዶ/ር ሙሉነህ ለማ ወ/ሰማያት የአርባ ምንጭ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ሳይንቲፊክ ዳይሬክተር ሆነው ተሹመዋል፡፡



ዶ/ር ሙሉነህ ለማ የ1ኛ ደረጃ ትምህርታቸው በፊንጫ 1ኛ ደረጃ ት/ቤት እንዲሁም የ2ኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በሻምቡ 2ኛ ደረጃ ት/ቤት በማጠናቀቅ በ1996 ዓ/ም ከአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በኤሌክትሪካል ምኅንድስና በመጀመሪያ ዲግሪ የተመረቁ ሲሆን 2ኛ ዲግሪያቸውን ዴልህ በሚገኘው “Indian Institute of Technology” በ “M.Tech power, Electronics, Electrical Machines and Drives” የትምህርት መስክ በ2002 ዓ/ም እንዲሁም 3ኛ ዲግሪያቸውን በደቡብ ኮሪያ ከሚገኘው “Pohang University of Science & Technology” በኤሌክትሪካል ምኅንድስና በ2010 ዓ/ም አጠናቀዋል፡፡

ዶ/ር ሙሉነህ የመጀመሪያ ዲግሪ ምርምራቸውን በ “Analysis & Design of Power Systems of Arba Minch University Campus”፣ የ2ኛ ዲግሪያቸውን “Analysis, Modeling & Control of Wind Energy Conversion System (WECS) Using DFIG” እና የ3ኛ ዲግሪ ማሟያ ምርምራቸውን እንዲሁ በ “Modeling & Verification of a Six – Phase Permanent Magnet Synchronous Motors used for Electric Vehicle Application” በሚሉ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ የተሠሩትን ጨምሮ 6 የምርምር ሥራዎችን በምርምር ጆርናሎች ላይ አሳትመዋል፡፡

ዶ/ር ሙሉነህ በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ እ.አ.አ ከሐምሌ ከ1997 – 1998 ዓ/ም በረዳት ምሩቅ፣ ከ1998 - 2002 ዓ/ም በሌክቸረር፣ ከ2010 ዓ/ም ጀምሮ በረዳት ፕሮፌሰር አካዳሚክ ማዕረግ እያገለገሉ ይገኛሉ፡፡ በተጨማሪም በአስተዳደር ዘርፍ ከመጋቢት 2000-2003 ዓ/ም የምኅንድስና ፋከልቲ ተባባሪ ሬጂስትራር፣ ከመስከረም 2003 – 2005 ዓ/ም የታዳሽ ኃይል ማዕከል ቴክኒካል ማኔጀር፣ ከየካቲት 2003 - 2005 የአርባ ምንጭ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት የተማሪዎች አገልግሎት ማዕከል አስተባባሪ፣ ከየካቲት 2011 – 2012 ዓ/ም የአርባ ምንጭ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት የምርምርና ማኅበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር፣ ከኅዳር 2012 – 2013 ዓ/ም የአርባ ምንጭ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ም/ሳይንቲፊክ ዳይሬክተር፣ ከኅዳር 2013 - መስከረም 2014 የታዳሽ ኃይል ቴክኖሎጂ ምርምር ማዕከል ዳይሬክተር፣ ከታኅሣሥ 2013 - መስከረም 2013 ዓ/ም ድረስ የአርባ ምንጭ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ሳይንቲፊክ ዳይሬክተር ተወካይ ሆነው ሲያገለግሉ ቆይተዋል፡፡

ዶ/ር ሙሉነህ በ2ኛው ዓለም አቀፍ የትምህርት ኤግዚብሽን የኤሌክትሪክ ባቡር አዲስ ዲዛይን በመሥራት የልዩ ዋንጫ ሽልማት አሸናፊ፣ ከኢትዮጵያ ትምህርት ሚኒስቴር ልዩ ሽልማት ያላቸው እንዲሁም በሀገር ደረጃ የኤሌክትሪክ ባቡር አዲስ ዲዛይን (Electric Train New Design) እና የኢንዳክሽን ሞተር (Induction Motor) በድምሩ የሁለት የፈጠራ ሥራ ፓቴንት ባለቤት ናቸው፡፡

መላው የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ማኅበረሰብ በቀጣይ የሥራ ዘመንዎ ስኬታማ እንዲሆኑ እየተመኘ የእንኳን ደስ አልዎት መልዕክቱን ያስተላልፋል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት