የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ባህልና ቋንቋ ጥናት ተቋም 2ኛውን ዓለም አቀፍ የኦሞቲክ ቋንቋ ዓውደ ጥናት ከጥቅምት 01-02/2014 ዓ.ም አካሂዷል፡፡ በዓውደ ጥናቱ ከሀገር ውስጥና ከውጭ ሀገራት በኦሞቲክ ቋንቋ ላይ የተሠሩ 17 ጥናቶች ቀርበው የቋንቋው ተናጋሪዎች ባሉበት ተገምግመዋል፡፡  ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ   

የዕለቱ የክብር እንግዳ የደ/ብ/ብ/ሕ/ክ/ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ተወካይ አቶ ዓለማየሁ ጌታቸው እንደገለጹት በአሁኑ ሰዓት የአፍ መፍቻ ቋንቋ ለትምህርት እየዋለ ቢሆንም አብዛኛዎቹ ቋንቋዎች የማጣቀሻ ቁሳቁስ፣ መዝገበ ቃላት፣ ሙያዊ የቃላት ስያሜና ሰዋሰው አልተሟላላቸውም፡፡ ክፍተቶቹን ለመሙላት በልዩ ልዩ የቋንቋ መስኮች ላይ ትኩረት አድርጎ በማጥናት ሀገራዊና ዓለም አቀፋዊ ጉባዔዎችን ማካሄድ የጎላ ፋይዳ ይኖረዋል፡፡

የዕለቱ ተጋባዥ እንግዳ በሚኒስትር ማዕረግ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የማኅበራዊ ጉዳይ አማካሪ ፕ/ር ሂሩት ወ/ማርያም በቁልፍ ንግግራቸው ኦሞቲክ ቋንቋ ገና ያልጠና፣ በአግባቡ ያልታወቀና በርካታ ግልጽ ያልሆኑ አከራካሪ ርዕሶች ያሉበት በመሆኑ ይህንን ለመፍታት የተደረጉት ጥናቶች ግልጽነት የጎደላቸው በመሆኑ መተቸታቸውን ተናግረዋል፡፡ ችግሩን ለመቅረፍ ኦሞቲክ አካባቢ ያሉ ዩኒቨርሲቲዎች ምርምሮችን በማካሄድ ብዥታዎችን ማጥፋትና ዕውቀት ላይ የተመረኮዘ ውሳኔ ላይ መድረስ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ እንደገለጹት ዩኒቨርሲቲው የተለያየ ቋንቋና ባህል ያለበት አካባቢ የሚገኝ በመሆኑ የክልሉን ብሎም የአካባቢውን ቋንቋ የማሳደግ ሥራ እየሠራ ይገኛል፡፡ ዩኒቨርሲቲው በአሁኑ ሰዓት የተለያዩ የማኅበራዊ ሳይንስ ት/ክፍሎችን በመክፈት የሠለጠኑ ባለሙያዎችን በማፍራት ላይ የሚገኝ ሲሆን በተጓዳኝ የባህልና ቋንቋ ጥናት ኢንስቲትዩት በመከፈቱ የበለጠ አዳዲስ ጥናቶችንና ሥራዎችን ለማከናወን ያግዛል ብለዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው የምርምርና ማኅበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዝደንት ተወካይ ዶ/ር ተስፋዬ ሀብተማሪያም በጉባዔው በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች በኦሞቲክ ቋንቋ የተሠሩ ምርምሮች እንደቀረቡ ገልጸው የኢትዮጵያ የብሄረሰብ ቋንቋ ፖሊሲዎችን ለመቃኘት እንዲሁም የከፊል ከሰሃራ በታች የአፍሪካ ሀገሮችን ቋንቋና ፖለቲካ ለመዳሰስ መድረኩ ጥሩ አጋጣሚ ነው ብለዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው የባህልና ቋንቋ ጥናት ኢንስቲትዩት ዳይሬክተር ዶ/ር ሰኢድ አሕመድ የኦሞቲክ ቋንቋ ከስያሜው ጀምሮ በሕዝብ፣ በመንግሥትም ሆነ በትምህርት ላይ ትኩረት ያላገኘ ጉዳይ በመሆኑ ልዩ ትኩረት እንዲሰጠውና የምርምር ቋንቋ እንዲሆን ከባለሙያዎችና ከሕብረተሰቡ ጋር በቅንጅት እየተሠራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ባህሎች አካዳሚ የባህል ተመራማሪ ፍሬሕይወት ባዩ በከፋ ዞን ውስጥ የሚኖሩ ጻራ ብሄረሰብ የስም አሰጣጥ፣ ክዋኔ እና ትርጉም ላይ ጥናታዊ ጽሑፍ አቅርበዋል፡፡ በጥናቱ እንደተመለከተው በብሄረሰቡ የተለያየ ስም አወጣጥ ያለ ሲሆን የመጀመሪያው እናት እንደወለደች አጠቃላይ ሁኔታውን መሠረት በማድረግ እንዲሁም ወንድ ልጅ በጉልበቱ ሠርቶ ስም እንዲወጣለት ያደርጋል፡፡ ሌላው ሴት ልጅ ስታገባ በባሏ ጎሳ ስም እንዲወጣላት የሚደረግ ሲሆን ጓደኞችም የጋራ ስም ያወጣሉ፡፡ በብሄረሰቡ መሰል ክዋኔዎች በጽሑፍ ያልተቀመጡ በመሆኑ በጥናት

እንዲታወቁ ማድረግ እንዲሁም ቋንቋው ከመጥፋቱ በፊት በአግባቡ ማጥናትና መሰነድ እንደሚገባ ጥናት አቅራቢዋ ሃሣብ ሰጥተዋል፡፡

በዓውደ ጥናቱ ከቀረቡ የጥናት ውጤቶች መካከል ‹‹Social Perception of linguistic Diversity in Gamo››፣ ‹‹language Policies for Nation Building in Ethiopia; looking back-looking forward››፣ ‹‹Mursi Construct Form Markers and the Information they Carry›› ለአብነት ይጠቀሳሉ፡፡

ከዚህ ቀደም የመጀመሪያው ዙር ዓውደ ጥናት በወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ የተደረገ ሲሆን 3ኛው ዙር በጂንካ ዩኒቨርሲቲ እንደሚካሄድ ተገልጿል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት