አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ እና “Christian Aid” የተሰኘ ግብረ ሠናይ ድርጅት በኢኖቬቲቭ እንሰት ፕሮጀክት የተሠሩ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን እንሰት አብቃይ በሆኑ አካባቢዎች ለሚገኙ አርሶ አደሮች ለማዳረስ መግባባት ላይ ደርሰዋል፡፡ ከድርጅቱ የመጡ የሥራ ኃላፊዎች ከዩኒቨርሲቲው አመራሮች ጋር በመሆን ጥቅምት 9/2014 ዓ/ም በዶርዜና ግርጫ ምርምር ማዕከላት ጉብኝት ያደረጉ ሲሆን በቅርቡም የመግባቢያ ስምምነት በመፈራረም ወደ ተግባር እንደሚገባ ታውቋል፡፡  ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ 

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ በጉብኝቱ ወቅት እንዳሉት በእንሰት ዙሪያ በዩኒቨርሲቲያችን ተመራማሪዎች የተገኙ ሳይንሳዊ የምርምር ውጤቶችና ቴክኖሎጂዎች የእንሰት ምርትና ምርታማነትን የሚያሳድጉ እንዲሁም የአመራረት ሂደቱን በማዘመን አላስፈላጊ የሥራ ድካሞችን የሚያስቀሩ በመሆናቸው ፋይዳቸው የጎላ ነው ብለዋል፡፡ የምርምር ውጤቶችንና አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ወደ ማኅበረሰቡ ማድረስ ትልቁ ግብ ነው ያሉት ዶ/ር ዳምጠው ከዚህ አንፃር ግብረ ሠናይ ድርጅቱ ከዩኒቨርሲቲው ጋር በትብብር ለመሥራት መምጣቱ አበረታች መሆኑንና ለሥራው ስኬት ዩኒቨርሲቲው አስፈላጊውን ሁሉ እንደሚያደርግ ጠቁመዋል፡፡

በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የባዮ ቴክኖሎጂ ተመራማሪና የቴክኖሎጂዎቹ የፈጠራ ባለቤት የሆኑት ዶ/ር አዲሱ ፈቃዱ እንሰት ላይ የተሠሩ ምርምሮችና የፈጠራ ሥራዎች የተለያዩ ዓለም አቀፋዊ፣ አህጉራዊና አገራዊ ሽልማቶችና ዕውቅናዎች የተገኙበት መሆኑን ጠቁመው ከሽልማቶቹና ዕውቅናዎቹ በላይ በቴክኖሎጂዎቹ ማኅበረሰቡ ሲጠቀምባቸውና ሕይወቱ ሲቀየር ማየት ትልቁ ሕልማቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በዚሁ መሠረት ቴክኖሎጂዎቹን ወደ ማኅበረሰቡ ለማዳረስ የተለያዩ አጋር አካላትን ለማግኘት ጥረት እየተደረገ መሆኑን የተናገሩት ዶ/ር አዲሱ “Christian Aid” የተሰኘው ግብረ ሠናይ ድርጅት ቴክኖሎጂዎቹን ወደ ማኅበረሰቡ ለማሸጋገር መስማማቱ ለሕልማችን ስኬት የበኩሉን ያበረክታል ብለዋል፡፡

የ “Christian Aid” የሀገር ውስጥ ዳይሬክተር አቶ ይጥና ተካልኝ ድርጅታቸው ዋና መሥሪያ ቤቱን እንግሊዝ ሀገር ያደረገ በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት የሚከሰቱ ችግሮችን መቅረፍ፣ የኅብረተሰቡን የአኗኗር ሁኔታ የተለያዩ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በማስፋፋት ማሻሻል እና ሰብዓዊ እርዳታዎችን ማድረስን ዓላማ አድርጎ የሚሠራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ እንሰት በመንግሥት ደረጃም ሆነ በምርምር ተቋማት ትኩረት ያላገኘና ከ25 ሚሊየን በላይ የሆኑ ኢትዮጵውያን የኑሮ መሠረት የሆነ ተክል መሆኑን የተናገሩት ዳይሬክተሩ በጉብኝታቸው አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በእንሰት ላይ የሠራቸው ምርምሮችና የፈጠራ ቴክኖሎጂዎች አበረታችና የማኅበረሰቡን አኗኗር የሚያሻሽሉ መሆናቸውን አረጋግጫለሁ ብለዋል፡፡ ድርጅታቸው በቅርቡ ከዩኒቨርሲቲው ጋር የመግባቢያ ስምምነት በመፈራረም እነዚህን አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች ለማኅበረሰቡ የማዳረስ ሥራ እንደሚሠራ የጠቆሙ ሲሆን በቀጣይም በውሃ፣ በአየር ንብረት ለውጥና በሌሎች ጉዳዮች ምርምርና ስርፀት ላይ ከዩኒቨርሲቲው ጋር እንሠራለን ብለዋለን፡፡

የዩኒቨርሲቲ ኢንደስትሪ ትስስርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ቶሌራ ሴዳ በበኩላቸው በእንሰት ዙሪያ የተሠሩ የቴክኖሎጂ ፈጠራ ሥራዎችን ወደ ማኅበረሰቡ ለማሸጋገር ከፍተኛ ፍላጎት መኖሩን ነገር ግን ቴክኖሎጂዎችን በስፋት ከማዳረስ አንፃር የበጀት ውስንነቶች እንደነበሩ ተናግረዋል፡፡ ከዚህም አንፃር አጋር ድርጅቶችን እየፈለግን ነበር ያሉት

ዶ/ር ቶሌራ “Christian Aid” በመስኩ በጋራ ለመሥራት በመምጣቱ እጅግ በጣም ደስተኛ መሆናቸውንና ለሥራው ስኬት ዳይሬክቶሬታቸው የበኩሉን ሚና ሁሉ እንደሚወጣ ተናግረዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ቴክኖሎጂዎቹን በተለያዩ ክልሎች እንሰት አብቃይ አካባቢዎች ለሚገኙ አርሶ አደሮች ለማዳረስ ከክልል ሴክተር መ/ቤቶች ጋር በቅርቡ የመግባቢያ ስምምነት እንደሚፈረምና በዩኒቨርሲቲው አቅምና ደረጃም ቴክኖሎጂዎቹን ለአካባቢው ማኅበረሰብ ለማዳረስ በትኩረት እየተሠራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በጉብኝትና በውይይት መርሃ-ግብሩ ላይ የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራሮች፣ የኮሌጅ ዲኖች፣ ዳይሬክተሮችና የዘርፉ ተመራማሪዎች የተገኙ ሲሆን ከሁለቱም ወገን የመግባቢያ ስምምነት የሚያዘጋጁ ግለሰቦች ተመርጠዋል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት