አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ከደቡብ ክልል ማዕድንና ኢነርጂ ኤጀንሲ ጋር በጋራ በመሆን በጋሞ ዞን አርባ ምንጭ ዙሪያ፣ ምዕራብ ዓባያ፣ ቁጫ፣ ጨንቻና ገረሴ ወረዳዎች ለማኅበረሰቡ የባዮ-ጋዝ ግንባታ ለማካሄድ መስከረም 4/2014 ዓ/ም የውል ስምምነት ሰነድ ተፈራርሟል፡፡ በዚህም መሠረት ከዩኒቨርሲቲው ለሥራ ማስፈፀሚያ 1,875,000 (አንድ ሚሊየን ስምንት መቶ ሰባ አምስት ሺህ) ብር እና የቁሳቁስ ድጋፍ እንዲሁም ማዕድንና ኢነርጂ ኤጀንሲ 4,054,115 (አራት ሚሊየን ሃምሳ አራት ሺህ አንድ መቶ አሥራ አምስት) ብር ድጋፍ አድርገዋል፡፡ ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ ዩኒቨርሲቲው ከምርምር፣ ከቴክኖሎጂ ሽግግርና ከማኅበረሰብ አገልግሎት አኳያ በርካታ ሀገራዊ፣ ክልላዊና ዞናዊ ሥራዎችን እየሠራ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡ በጋራ የሚሠሩ ሥራዎች ተፈፃሚነት እንዲያገኙ ልዩ ትኩረት ማድረግ ያስፈልጋልም ብለዋል፡፡

የደቡብ ክልል ማዕድንና ኢነርጂ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ አፀደ አይዛ እንደገለጹት ኤጀንሲያቸው የማዕድን አለኝታ ጥናት በማስጠናት ከተለያዩ የምርምር ተቋማት ጋር በመናበብ ጥናት የሚያካሂድ ሲሆን ወጣቶችን በማደራጀት ቴክኖሎጂዎችን ለኅብረተሰቡ ያዳርሳል፡፡ ኤጀንሲው ከአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ጋር በማዕድን ላይ ሰፊ ሥራዎችን እየሠራ እንደሚገኝ የተናገሩት ዋና ዳይሬክተሯ በዚህ ስምምነት ለ250 የቤት እመቤቶች የባዮ-ጋዝ ግንባታ ለማካሄድ ታቅዷል ብለዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲ-ኢንደስትሪ ትስስርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ቶሌራ ሴዳ በበኩላቸው ላለፉት አምስት ዓመታት የማዕድን አለኝታ ጥናት በስፋት መካሄዱን ጠቁመው በዘርፉ ለማኅበረሰቡ ትርጉም ያለው ሥራ መሠራቱንና እንደ ባለሙያ ዕውቀትን ማሸጋገር እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡

የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ሳይቲፊክ ዳይሬክተር ዶ/ር ሙሉነህ ለማ እንደገለጹት ዩኒቨርሲቲው ካሉት የልህቀት ማዕከላት መካከል የታዳሽ ኃይል ምርምር ማዕከል አንዱ ሲሆን በዋናነት በአማራጭ ኃይል አቅርቦት ላይ ይሠራል፡፡ በዚህም የኤሌክትሪክ ኃይል የማያገኙና ራቅ ያሉ የገጠር ትምህርት ቤቶችን ተጠቃሚ አድርጓል ብለዋል፡፡

በውል ስምምነቱ መርሃ-ግብር የደቡብ ክልል ማዕድንና ኢነርጂ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተርና ባለሙያዎች፣ የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራሮችና የጋሞ ዞን ውሃ፣ ማዕድንና ኢነርጂ ቢሮ ባለሙያዎች ተገኝተዋል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት