የአርባ ምንጭ ቴክኖሎጂና ውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩቶች ሴቶች፣ ሕፃናትና ወጣቶች ማስተባበሪያ ጽ/ቤት በ2013 ዓ.ም በዋናው ግቢ ለተመደቡ የመጀመሪያ ዓመት 600 ወንድ ተማሪዎች መስከረም 14/2014 ዓ.ም የማነቃቂያና የልምድ ልውውጥ መድረክ አዘጋጅቷል፡፡ ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

በመድረኩ የ5ኛ ዓመት ተመራቂ ተማሪዎች በቆይታቸው ወቅት ያገኙትን ልምድ ያካፈሉ ሲሆን በት/ክፍል መረጣ፣ በምዝገባና በማጠቃለያ ፈተና ጊዜ ሊኖር በሚገባው ጥንቃቄ ዙሪያ ገለጻ ተደርጓል፡፡

የኢንስቲትዩቶቹ ሴቶች፣ ሕፃናትና ወጣቶች ማስተባበሪያ ጽ/ቤት የወጣቶች ዘርፍ አስተባባሪ ወ/ሮ አበበች አዳነ እንደገለጹት የልምድ ልውውጥ መድረኩ ከዚህ ቀደም በኢንስቲትዩቶቹ ለተመደቡ ሴት ተማሪዎች የተዘጋጀ ሲሆን በዚህኛው ዙር ለወንድ ተማሪዎች ተዘጋጅቷል፡፡ ዓላማውም ተማሪዎች በግቢ ቆይታቸው ከተለያዩ ሱሶች የጸዱና ከአልባሌ ቦታ ተጠብቀው በትምህርታቸው ውጤታማ እንዲሆኑ ማስቻል ነው ብለዋል፡፡

የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት የጋራ ኮርሶች አስተባበሪ አቶ ገብሬ ፍሬው ስለ ትምህርት ክፍል መረጣ ገለጻ ሲያደርጉ የት/ክፍሉን የመቀበል አቅም ባገናዘበ መልኩ ሁሉንም ተማሪዎች በመረጡት ት/ክፍል ለመመደብ ጥረት ይደረጋል ብለዋል፡፡ ምዝገባ ያላጠናቀቁ ተማሪዎች በአስተባባሪዎች በኩል ምዝገባ እንዲያከናውኑም አሳስበዋል፡፡

የ5ኛ ዓመት የኤሌክትሪካልና ኮምፕዩተር ኢንጂነሪንግ ተመራቂ ተማሪ ፀጋዬ አረጋ ተሞክሮውን ሲያካፍል በዩኒቨርሲቲ የሚኖራቸው ቆይታ ስኬታማ እንዲሆን ከቤተሰብ ክትትል የራቁ በመሆኑ ራሳቸውን መቆጣጠር፣ ጊዜን በአግባቡ መጠቀም፣ በዕቅድ መመራትና ጓደኛ አመራረጥ ላይ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ተናግሯል፡፡

የመጀመሪያ ዓመት ተማሪ ይበልጣል ዘርይሁን ከመድረኩ በጊዜ አጠቃቀም፣ በፈተና ጊዜ ጥንቃቄና በሌሎችም ጉዳዮች ላይ ጠቃሚ ሃሳቦችን መጨበጡን ገልጿል፡፡