AMU-IUC ፕሮግራም ከአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ሴቶች፣ ሕፃናትና ወጣቶች ዳይሬክቶሬት ጋር በመተባበር ፕሮጀክቱ በሚሰጠው ነፃ የ3ኛ ዲግሪ የትምህርት ዕድል የሴቶች ተሳትፎ እንዲጨምር ለሴት መምህራን ከጥቅምት 18-19/2014 ዓ/ም የግንዛቤ ማስጨበጫ ውይይት አዘጋጅቷል፡፡ ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ተክሉ ወጋየሁ ሴት መምህራን ጠንክረው ከሠሩና ከተደገፉ የትኛውንም ሥራ መሥራት እንደሚችሉ ጠቅሰው በዩኒቨርሲቲውም ሴት ተማሪዎች በየደረጃው እስከ ወርቅ ሜዳሊያ ተሸላሚ በመሆን ብቃታቸውን እያሳዩ ነው ብለዋል፡፡

የAMU-IUC ፕሮግራም አስተባባሪ ዶ/ር ፋሲል እሸቱ እንደገለጹት ፕሮግራሙ የሁለት ዙር መርሃ-ግብር ያለው ሲሆን በመጀመሪያ ዙር 19 የዩኒቨርሲቲውን መምህራን በ3ኛ ዲግሪ አስተምሮ በማጠናቀቅ ላይ ይገኛል፡፡ ፕሮግራሙ ለመምህራኑ የትምህርትና የምርምር ቁሳቁስ እንዲሁም ቤተ-ሙከራዎችን በማሟላት እንዲገለገሉ ያደረገ ሲሆን ለዩኒቨርሲቲውም መኪናን ጨምሮ በርካታ ቁሳቁሶችን ድጋፍ አድርጓል፡፡

እንደ ዶ/ር ፋሲል ገለጻ ፕሮግራሙ ከሚሰጠው የትምህርት ዕድል 60 በመቶው ለሴት መምህራን ቢሆንም የሴቶች ተሳትፎ እጅግ አናሳ ነው፡፡ ተሳትፏቸውን ለማሳደግ መረጃው ቀድሞ እንዲደርሳቸውና ሥልጠናዎችን በማመቻቸት ብቁ ለማድረግ እየሠራን ነው ብለዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ሴቶች፣ ሕፃናትና ወጣቶች ጉዳይ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወ/ሪት ሠናይት ሳህሌ እንደገለጹት ሴት መምህራን 3ኛ ዲግሪ ትምህርት መማራቸው ወደ ማኅበረሰቡ በመውረድ ለሴቶች ዘርፈ-ብዙ ችግሮች መፍትሔ የሚሰጡ ምርምሮችን እንዲሠሩ ዕድል የሚሰጥ ነው፡፡ በሴት መምህራን በኩል አቅም ቢኖርም የተነሳሽነት ማነስ የሚስተዋል በመሆኑ ውይይቱ በፕሮግራሙ የተማሩ ሴት መምህራንን በማቅረብ የትኛውንም ችግርና ቤተሰባዊ ኃላፊነት ተቋቁመው ማለፍ እንደሚችሉ ለማሳየት የተዘጋጀ መሆኑን ዳይሬክተሯ ተናግረዋል፡፡

ሴት መምህራን በርካታ ኃላፊነቶች ያሉባቸው መሆኑን የተናገሩት ተወያዮቹ መሰል ዕድሎች ሴት መምህራን የተሻለ የትምህርት ደረጃ እንዲኖራቸው የሚያግዙ በመሆኑ መረጃዎችን በመለዋወጥና ተደጋግፎ በመሥራት የሚፈለገውን ግብ ለመምታት ልንሠራ ይገባል ብለዋል፡፡

በውይይቱ 67 ሴት መምህራን የተሳተፉ ሲሆን በAMU-IUC እና በመሰል ፕሮግራሞች ተሳታፊ ሆነው የተመረቁና ለምረቃ እየተቃረቡ የሚገኙ ሴት መምህራን ልምዳቸውን አካፍለዋል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት