በአርባ ምንጭ ከተማ ለሚገነባው የአረጋውያንና ሕፃናት ማዕከል ገቢ ማሰባሰቢያ ‹‹ኑ የነገ ቤታችንን እንሥራ›› በሚል መሪ ቃል መስከረም 11/2014 ዓ/ም በአርባ ምንጭ ከተማ የማነቃቂያ የእግር ጉዞ ተካሂዷል፡፡ ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

መርሃ-ግብሩ በቅርቡ በአርባ ምንጭ ከተማ ግንባታው ለሚጀመረው የአረጋውያንና ሕፃናት ማዕከል ገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራም ለማስጀመርና ማኅበረሰቡን ለማነቃቃት የተዘጋጀ መሆኑን የሜሪ ጆይ-ኢትዮጵያ መሥራችና ሥራ አስኪያጅ ሲስተር ዘቢደር ዘውዴ ተናግረዋል፡፡ በ7,800 ካሬ ሜትር ቦታ ላይ የሚያርፈው ማዕከል ከጥቂት ሳምንታት በኋላ ግንባታው ይጀመራል ያሉት ሥራ አስኪያጇ ለዚህም የማዕከሉ የዲዛይን ሥራ መጠናቀቁንና ለግንባታ ማስጀመሪያ የሚውል ከ7 ሚሊየን ብር በላይ መሰብሰቡን ጠቁመዋል፡፡

የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ ባስተላለፉት መልዕክት ኢትዮጵያውያን ነፃነታችንን ጠብቀን የኖርነው ጀግኖች አባቶቻችን በዋሉልን ውለታ መሆኑን ጠቁመው በአርባ ምንጭ ከተማ የሚገነባው ማዕከልም እነዚህን የሀገር ባለውለታ አባቶቻችንን የምንንከባከብበት ነው ብለዋል፡፡ የጋሞ አባቶች የትውልድን አንድነትና የአካባቢን ሰላም ጠብቆ የመቆየት እሴቶች ወደ ቀጣዩ ትውልድ እንዲተላለፉ ማዕከሉ ጉልህ ሚና የሚጫወት በመሆኑ ለማዕከሉ ግንባታ የአካባቢው ማኅበረሰብ የበኩሉን ሊወጣ እንደሚገባውም ዶ/ር ኤርጎጌ ተናግረዋል፡፡

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ማዕከሉ ተገንብቶ እስኪጠናቀቅ ድረስ ከጋሞ ዞንና ከአርባ ምንጭ ከተማ አስተዳደር ጋር በመሆን አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልጸው ለመነሻ ያህል ዩኒቨርሲቲው 8 መቶ ሺህ ብር ለማበርከት ቃል መግባቱን ተናግረዋል፡፡ በማዕከሉ የግንባታ ሂደትና ተጠናቆ ሥራ ሲጀምርም ዩኒቨርሲቲው አስፈላጊውን ሙያዊና የቁሳቁስ ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል፡፡

የጋሞ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ብርሃኑ ዘውዴ በበኩላቸው ማዕከሉ ለሀገራቸው ውለታ የዋሉ አረጋውያን የሚጦሩበት በመሆኑ ለግንባታው ሁላችንም የበኩላችንን ልንወጣ ይገባል ብለዋል፡፡ አጋርነታቸውን ለመግለጽ በመርሃ ግብሩ ላይ ለተገኙ ሁሉ በዞኑ ስም ምሥጋና አቅርበዋል፡፡

በዕለቱ በሜሪ ጆይ ኢትዮጵያ፣ በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ፣ በጋሞ ዞን አስተዳደር፣ በአርባ ምንጭ ከተማ አስተዳደርና በጋሞ ዞን ኮንስትራክሽንና ከተማ ልማት መምሪያ ማዕከሉን በጋራ ለመሥራት የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት በፓራዳይዝ ሎጅ ተፈርሟል፡፡ በስምምነቱ መሠረት 5ቱ ተቋማት የማዕከሉ ግንባታ ተጀምሮ እስኪጠናቀቅ በሙያ፣ በገንዘብ፣ በቁሳቁስ እንዲሁም ማኅበረሰቡን አስተባብሮ ሀብት በማሰባሰብ ረገድ በትብብር ይሠራሉ፡፡

በመርሃ-ግብሩ ደራሲ ሜሪ ጃፋር ለ130 ዓመታት የቆየ 41 ግራም ወርቅ ለግንባታው ገቢ ማሰባሰቢያ እንዲውል ያቀረበች ሲሆን በዕለቱ የተገኙ የግል ባለሀብቶችና ድርጅቶች ለግንባታው ስኬት የሚውል የገንዘብና የቁሳቁስ ድጋፍ ለማድረግ ቃል ገብተዋል፡፡ የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የተማሪዎች ኅብረትም የማዕከሉ ግንባታ ተጀምሮ እስኪጠናቀቅ ጊዜ ድረስ በየሴሚስተሩ የ1 ቀን የሥጋ ፕሮግራምን ወደ ሽሮ በመቀየር የገንዝብ ድጋፍ እንደሚያደርግ ቃል ገብቷል፡፡

በእግር ጉዞ ፕሮግራሙ የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ፣ የሜሪጆይ ኢትዮጵያ መሥራችና ሥራ አስኪያጅ ሲስትር ዘቢደር ዘውዴ፣ የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛና የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራሮችና ማኅበረሰብ፣ የጋሞ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ብርሃኑ ዘውዴ፣ የአርባ ምንጭ ከተማ ከንቲባ አቶ ሰብስቤ ቡናቤ፣ አርቲስት ፋንቱ ማንዶዬ፣ አርቲስት አብራር አብዶ፣ ደራሲ ሜሪ ጃፋር፣ የጋሞ አባቶችና የአርባ ምንጭና አካባቢው ነዋሪዎች ተሳትፈዋል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት