የኢትዮጵያ መምህራን ማኅበር ከአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ‹‹Teachers at the Heart of Education Recovery›› በሚል መሪ ቃል ከጥቅምት 18-19/2014 ዓ/ም የዓለም መምህራን ቀንን ምክንያት በማድረግ ኮንፈረንስ አካሂዷል፡፡ ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የኢትዮጵያ መምህራን ማኅበር ፕሬዝደንት ዶ/ር ዮሐንስ በንቲ መምህራን ለአንድ ሀገር እድገት ወሳኝ ሚና እንዳላቸው ጠቁመው መምህራን ትውልድን ከመቅረጽ አኳያ የተማሪዎችን ፍላጎት መለየትና ተሰጥኦዋቸውን እንዲያወጡ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል ብለዋል፡፡ ዘላቂ ሰላምና ወንድማማችነት ሊጎለብትና በመጪው ትውልድ አዕምሮ ውስጥ ሊቀረጽ የሚችለው ትምህርትን ለሁሉም ወገኖች ተደራሽ በማድረግ እንደመሆኑ ለመምህራንና ለትምህርት አስፈላጊው ሀብት ሊመደብ እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ አስተዳደር ጉዳዮች ም/ፕሬዝንት እና የፕሬዝደንቱ ተወካይ ዶ/ር መልካሙ ማዳ ዓለም ዓቀፉን የመምህራን ቀን ከመቶ ሀገራት በላይ በተለያዩ ዝግጅቶች እንደሚያከብሩ ጠቅሰው ቀኑ በሀገራችንና በዩኒቨርሲቲው መታሰቡ በትምህርት ጥራት፣ በአዲሱ የትምህርት ፍኖተ ካርታ መሠረት የተዘጋጀው ጥናት ወደ ተግባር መግባት በሚችልበት ሁኔታ እንዲሁም በወቅታዊ ግጭትና በኮቪድ-19 ምክንያት ከትምህርት ገበታ ውጭ የሆኑ ተማሪዎችና ከመምህራን የሚጠበቅ ኃላፊነት ዙሪያ ለመወያየት ዕድል የሚሰጥ ነው ብለዋል፡፡

በኮንፈረንሱ ‹‹ያለ ሰላም ትምህርት፤ ያለ ትምህርት ሰላም››፣ ‹‹የግል ትምህርት ቤቶች ያላቸው አስተዋጽኦና የሚሰጣቸው ትርጓሜ››፣ ‹‹በዝቅተኛ የትምህርት ደረጃ ላይ የሚገኙ ት/ቤቶች የትምህርት ጥራትን ከማስጠበቅ አኳያ እየሠሩ ያለው ሥራ››፣ ‹‹ኮቪድ-19 በተማሪ አሳታፊ የመማር ማስተማር ሥነ-ዘዴ ውስጥ እየፈጠረ ያለው አሳሳቢነት››፣ ‹‹ፖለቲካና ትምህርት በኢትዮጵያ›› የሚሉና ሌሎችን ጨምሮ በአጠቃላይ 16 ጥናታዊ ጽሑፎች ቀርበዋል፡፡

በፕሮግራሙ ማጠቃለያ በኦሮሚያ ክልል ሰበታ ከተማ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት የሂሳብ መምህርት የሆኑት መ/ርት ትህትና ብሥራት በሀገሪቷ ውስጥ ካሉ መምህራን የላቀ አፈጻጸም በማስመዝገብ የዓመቱ ምርጥ መምህርት በመሆን የሜዳሊያ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል፡፡

በኮንፈረንሱ ከተለያዩ የሀገሪቷ ክፍሎች የመጡ የመምህራን ማኅበር ሥራ አስፈጻሚዎች፣ የተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ተቋም (UNESCO) ተወካይ፣ የትምህርት ሚኒስቴርና የተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ሥራ አስፈጻሚዎችና ተወካዮች ታድመዋል፡፡

ከኮንፈረንሱ አንድ ቀን ቀደም ብሎ ጥቅምት 17/2014 ዓ/ም የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የመምህራን ማኅበርን ለቀጣዮቹ 4 ዓመታት የሚመሩ ሥራ አስፈጻሚዎች ምርጫ የተከናወነ ሲሆን አቶ ጋሻው ዓለሙ ከቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት የማኅበሩ ፕሬዝደንት፣ አቶ መለሰ ተሾመ ከማኅበራዊ ሳይንስና ሥነ-ሰብ ኮሌጅ ም/ፕሬዝደንት፣ ዶ/ር ኤሊያስ ገብሩ ከውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ጸሐፊ፣ አቶ አበበ ፈቃዱ ከግብርና ሳይንስ ኮሌጅ የሕዝብ ግንኙነት፣ አቶ ጌታሰው አንለይ ከተፈጥሮና ቀመር ሳይንስ ኮሌጅ የሥርዓተ-ትምህርትና ሥልጠና ተወካይ እንዲሁም ወ/ሮ ስንታየሁ አበበ ከሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የሥርዓተ-ፆታ ተጠሪ ሆነው ተመርጠዋል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት