የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ማኅበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት በአርባ ምንጭ ከተማ መንገድ ዳር ካሉና ለትራፊክ አደጋ ተጋላጭ ከሆኑ 10 ትምህርት ቤቶች ለተወጣጡ 60 የተማሪ ትራፊክ ፖሊሶች ጳጉሜ 3/2013 ዓ/ም የደንብ ልብስ ድጋፍ አድርጓል፡፡  ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ ተማሪዎቹ ሕዝብን ለማገልገል በፍላጎት መነሳሳታቸውን አድንቀው በትምህርታቸው እንዲበረቱና ጎን ለጎንም በጎ ሥራቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው የማኅበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ተክሉ ወጋየሁ በበኩላቸው የአርባ ምንጭ ከተማ የትራፊክ ደኅንነት ጽ/ቤት ያቀረበውን የድጋፍ ጥያቄ ተገቢነቱንና አስፈላጊነቱን በመረዳት በአጭር ጊዜ ውስጥ አስተናግደናል ብለዋል፡፡ ለደንብ ልብሱ ግዢ 30,000(ሠላሳ ሺህ)ብር ወጪ መደረጉንም ተናግረዋል፡፡

የአርባ ምንጭ ከተማ መንገድ ትራንስፖርት ልማት ጽ/ቤት የትምህርትና ሥልጠና ግንዛቤ የመፍጠር ሥራ ሂደት ባለሙያ አቶ በቀለ ወንድሙ እንደገለጹት በትራፊክ አደጋ እየደረሰ ያለውን የዜጎች ሞት በተለይም ተማሪዎች ትምህርት ቤት በሚገቡበትና በሚወጡበት ጊዜ የሚደርሰውን አደጋ ለመቀነስ ተጋላጭ ከሆኑ ትምህርት ቤቶች የተማሪ ትራፊክ ፖሊሶች ተመልምለው ለ1 ወር ከ15 ቀን ፖሊሳዊና የተግባር ሥልጠና ወስደዋል፡፡ ሥልጠናው ተማሪዎቹ ራሳቸውንና ሌሎችንም ከአደጋ እንዲታደጉና ተማሪዎችን በአግባቡ እንዲያገለግሉ በቂ ግንዛቤ ያገኙበት መሆኑን የገለጹት አቶ በቀለ በቀጣይም በትምህርት ቤት ደረጃ አጫጭር ሥልጠናዎችን በመስጠት ድጋፍ እንዲያደርግ ጠይቀዋል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት