የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ 1 የ3ኛ ዲግሪና 7 የ2ኛ ዲግሪ ትምህርት ፕሮግራሞችን ለመክፈት የሚያስችለውን የውጭ ሥርዓተ-ትምህርት ግምገማ የዘርፉ ምሁራን በተገኙበት ከመስከረም 6 - 7/2014 ዓ/ም አካሂዷል፡፡  ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ 

በማኅበረሰብ ጤና ት/ክፍል ‹‹PhD in Public Health››፣ ‹‹MPH in Health Service Management›› እና ‹‹MPH in Health Promotion and Behavioral Science››፤ በነርሲንግ ት/ክፍል ‹‹MSc in Adult Health Nursing››፣ ‹‹MSc in Neonatal Nursing››፣ ‹‹MSc in Pediatric and Child Health Nursing››፤ በሕክምና ት/ቤት ‹‹MSc in Medical Physiology›› እንዲሁም በሜዲካል ራዲዮሎጂ ቴክኖሎጂ ት/ክፍል ‹‹MSc in Medical Radiologic Technology›› የተሰኙ ፕሮግራሞች በኮሌጁ ለውጭ የሥርዓተ-ትምህርት ግምገማ የቀረቡ ናቸው፡፡

የአካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር ዓለማየሁ ጩፋሞ እንደተናገሩት አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የምርምር ዩኒቨርሲቲ እንደ መሆኑ የተለያዩ ምርምር ተኮር ፕሮግራሞችን በ2ኛና 3ኛ ዲግሪ መርሃ-ግብሮች በመክፈት ላይ ይገኛል፡፡ እንደ ም/ፕሬዝደንቱ ገለጻ የምርምር ዩኒቨርሲቲዎች ውጤታማነት የሚለካው በ2ኛና በ3ኛ ዲግሪ ትምህርት ፕሮግራሞች ምርምር ገለጻ፣ ክንውንና ስኬት መሆኑ በሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር አፅንኦት የተሰጠው ነው፡፡ ስለዚህም እያንዳንዱ የዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ ለፕሮግራሞቹ ስኬት የበኩሉን በጎ ተፅዕኖ ማሳደር ይጠበቅበታል ብለዋል፡፡

የድኅረ ምረቃ ትምህርት ቤት ዳይሬክተር ዶ/ር አበራ ኡንቻ እንደገለጹት በ2014 በጀት ዓመትና በቀጣይ ጥቂት ዓመታት ውስጥ በሁሉም ፋከልቲዎችና ት/ክፍሎች በተለያዩ መስኮች በርካታ የ2ኛና የ3ኛ ዲግሪ ፕሮግራሞችን ማስጀመር ላይ ትኩረት ለማድረግ ታቅዷል፡፡ የ2ኛ ዲግሪ ፕሮግራሞችን በ2 ዓመት እና የ3ኛ ዲግሪ ፕሮግራሞችን በ4 ዓመታት ማጠናቀቅ ሌላው በትኩረት ሊሠራ የሚገባው ጉዳይ መሆኑንም ዳይሬክተሩ ጠቅሰዋል፡፡

ዶ/ር አበራ አክለው እንደተናገሩት ይህን ግብ ለማሳካት የሚጥሩ ዘርፎችን ለመደገፍና ለማበረታታት የድኅረ ምረቃ ት/ቤት በኃላፊነት ይሠራል፡፡ በዚህ ረገድ የሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ከት/ክፍሎች ጋር በኅብረት በመሥራት 8 ፕሮግራሞችን ለመገምገም መብቃቱ የሚደነቅ ነው፡፡ በግምገማው የተሰጡ አስተያየቶችም ሥርዓተ-ትምህርቱ ደረጃውን የጠበቀ እንዲሆን የጎላ ሚና ይኖራቸዋል፡፡

የሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ቺፍ ኤክስኪዩቲቭ ዳይሬክተር ዶ/ር ታምሩ ሽብሩ በበኩላቸው ኮሌጁ 7 የ2ኛ ዲግሪና 1 የ3ኛ ዲግሪ ትምህርት ፕሮግራሞች የውጭ የሥርዓተ-ትምህርት ግምገማ ማካሄዱን ገልጸው በ3ኛ ዲግሪ መርሃ-ግብር ለግምገማ የቀረበው ፕሮግራም በኮሌጁ ታሪክ የመጀመሪያው ነው ብለዋል፡፡ ለግምገማ የቀረቡትን 8 ፕሮግራሞች አስመልክቶ ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች የዳሰሳ ጥናት ተደርጎ የፕሮግራሞቹ አስፈላጊነትና ፋይዳ የተረጋገጠ ሲሆን እያንዳንዱን ፕሮግራም ሁለት ሁለት ከአቻ ዩኒቨርሲቲዎች የመጡ በሙያው ልምድ ያላቸው የዘርፉ ምሁራን መገምገማቸውን ዶ/ር ታምሩ ተናግረዋል፡፡

በፕሮግራሙ የዩኒቨርሲቲው አመራሮች፣ ከአቻ ዩኒቨርሲቲዎች የመጡ ገሚጋሚዎች፣ የኮሌጁ የትምህርትና የሥራ ክፍል ኃላፊዎች፣ የኮሌጅ ዲኖችና መምህራን ተገኝተዋል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት