ግብርና ሳይንስ ኮሌጅ ከ “GIZ” ጋር በመተባበር ወጣቶችን በትምህርት ቤት በማሳተፍ በጫሞ ሐይቅ ተፋሰስ የመሬት መራቆትና የአፈር መሸርሸርን ለመከላከልና የተራቆቱና የተጎዱ ሥነ-ምኅዳሮችን መልሶ ለማቋቋም በሚያስችል ፕሮጀክት ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ጥቅምት 27/2014 ዓ/ም ውይይት አካሂዷል፡ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የጫሞ ተፋሰስ ከከፍታ ቦታ ጀምሮ ተፋሰሱን ይዞ እስከ ሐይቁ ድረስ ያሉ መሠረታዊ ችግሮች፣ ችግሮቹን ለመቅረፍ ዩኒቨርሲቲው ከባለድርሻ አካላት ጋር እየሠራ ያለው ሥራ፣ በተፋሰሱ ዙሪያ ያሉ የማኅበረሰብ ክፍሎች ስጋትና መፍትሄው እንዲሁም ከባለድርሻ አካላት የሚጠበቁ ተግባራት ውይይቱ ካተኮረባቸው ነጥቦች መካከል ናቸው፡፡

የግብርና ሳይንስ ኮሌጅ ዲን ዶ/ር ብርሃኑ ለማ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣው የመሬት መራቆትና የአፈር መሸርሸር ምርትና ምርታማነት በእጅጉ እንዲቀንስና የውሃ ዕጥረት እንዲከሰት የጎላ አስተዋጽኦ እንዳለው ገልጸው የተራቆተውን መሬት መልሶ እንዲያገግምና ወደ ቀድሞው ቦታው እንዲመለስ በሚተገበረው የደን ጥበቃ ፕሮጀክት ላይ የወጣቶችን አቅም መጠቀም አስፈላጊ ነው ብለዋል፡፡ በተለይም ከት/ቤቶች ጋር በቅንጅት በመሥራት በዛፍና ደን ጥቅም፣ በአየር ንብረት፣ በግብርና ምርትና የአካባቢ ሥነ-ምኅዳር ዙሪያ ግንዛቤ እንዲያገኙ ማስተማር እንደሚገባ የኮሌጁ ዲን ተናግረዋል፡፡

በግብርና ሳይንስ ኮሌጅ የፎርስትሪ ት/ክፍል መምህርና የሰነዱ አቅራቢ አቶ አስመላሽ ተስፋዬ ካለፉት 3 ዓመታት ጀምሮ በጀርመን መንግሥት በሚደገፈውና በአካባቢ ጥበቃ ላይ በሚሠራው “GIZ” እና ከአካባቢና የተፈጥሮ ሀብት ጋር በተያያዙ ሴክተር መሥሪያ ቤቶች እንዲሁም በኅብረተሰቡ ድጋፍ የተጎዱ ቦታዎችን የማልማት ሥራዎች ሲሠሩ መቆየታቸውን ገልጸዋል፡፡ በት/ቤቶች ውስጥ ያሉ የሀገር ተረካቢ ወጣቶች የተራቆቱ አካባቢዎችን ለማልማት በፕሮጀክቱ መሳተፋቸው የመፍትሄ አካል ከመሆን ባለፈ በአካባቢ ጥበቃ ላይ በዘላቂነት እንዲሠሩ በቂ ግንዛቤ እንዲኖራቸው ያግዛል ብለዋል፡፡ ፕሮጀክቱን ለመጀመር በሚያስፈልጉ ቅድመ ሁኔታዎች ላይ ከስምምነት ለመድረስ ውይይቱ ማስፈለጉን አቶ አስመላሽ ተናግረዋል፡፡

ፕሮጀክቱ የጫሞ ተፋሰስ አጎራባች አካባቢዎችን ሥነ-ምኅዳር በጠበቀ መልኩ በተመረጡ 3 ት/ቤቶች በአርባ ምንጭ ከተማ ጫሞ፣ ገረሴ ወረዳ ዛዜ እና ደምባ ጾሳ 1ኛ ደረጃ ት/ቤቶች የሚተገበር ሲሆን 1 ሚሊየን ብር በጀት ተመድቦለት በቀጣዮቹ 8 ወራት ውስጥ የሚጠናቀቅ ይሆናል፡፡

በውይይቱ የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ አመራሮች፣ የጋሞ ዞን የደንና አየር ንብረት ለውጥ ጽ/ቤት ኃላፊዎች፣ የጋሞ ዞን የትምህርት ልማት መምሪያ ኃላፊዎች፣ የገረሴ ወረዳ የአስተዳደር፣ የትምህርት፣ የአካባቢ ደንና አየር ንብረት ለውጥ ልማት ጽ/ቤት ኃላፊዎች እንዲሁም በዞኑ ውስጥ ከሚገኙ የተመረጡ የመጀመሪያ ደረጃ ት/ቤቶች የመጡ ርዕሳነ መምህራን ታድመዋል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት