የዩኒቨርሲቲ-ኢንደስትሪ ትስስርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ዳይሬክቶሬት የኅብረተሰቡን ችግር ሊፈቱ የሚችሉና በኢንደስትሪና ቴክኖሎጂ ዘርፍ ላይ ያተኮሩ 15 የምርምር ንድፈ ሃሳቦች ግምገማ ጥቅምት 30/2014 ዓ/ም አካሂዷል፡፡ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

ከቀረቡት የምርምር ንድፈ ሃሳቦች መካከል ተሻሽሎ የቀረበ የአረም ማጥፊያ መሳሪያ፣ ከማዳበሪያ ጋር በማገናኘት ጤፍ የሚዘራ ማሽን፣ ለግብርና ሥራ የሚውል አነስተኛ ትራክተር፣ በኤሌክትሪክ ኃይል የሚሠራ የወተት መናጫ፣ ማንጎ መሰብሰቢያ፣ እንጀራ ሳይሻግት ለረጅም ጊዜ ማቆየት የሚያስችል ማሽንና ሌሎች የተለያዩ የሰው ጉልበት መቆጠቢያ ማሽኖች የማዘጋጃ ንድፈ ሃሳቦች ይጠቀሳሉ፡፡

የዳይሬክቶሬቱ ዳይሬክተር ዶ/ር ቶሌራ ሴዳ የተጀመሩና አዳዲስ የሚፈጠሩ ቴክኖሎጂዎችን ለኅብረተሰቡ ተደራሽ ለማድረግ ዩኒቨርሲቲው በቴክኖሎጂው ዘርፍ ከሚንቀሳቀሱ አካላት ጋር ቁርኝት መፍጠሩ የጎላ ሚና እንዳለው ገልጸዋል፡፡ የቴክኖሎጂ ውጤቶች እንዲጠናከሩና ወደ ሚፈለግበት ደረጃ እንዲደርሱ በጥናትና ምርምር ላይ መመሥረት ውጤታማ ሥራዎች እንዲሠሩ የሚያግዝ ነውም ብለዋል፡፡ ከቀረቡት የምርምር ንድፈ ሃሳቦች መካከል የተሻሉና የኅብረተሰቡን ችግር ሊፈቱ የሚችሉ ተለይተው ወደ ማኅበረሰቡ እንዲወርዱ እንደሚደረግ ዶ/ር ቶሌራ ተናግረዋል፡፡

ንድፈ ሃሳቡን 15 መምህራን ያቀረቡ ሲሆን 30 የዘርፉ ተመራማሪዎች በግምገማው ተሳትፈዋል፡፡ በፕሮግራሙም የዩኒቨርሲቲውና ከአርባ ምንጭ ቴክኒክና ሙያ ትምህርት ኮሌጅ የመጡ መምህራንና ተመራማሪዎች ተገኝተዋል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት