የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ሴቶች፣ ሕፃናትና ወጣቶች ዳይሬክቶሬት ለሳውላ ካምፓስ የአስተዳደር ሠራተኞች በሥርዓተ-ጾታና ጾታዊ ትንኮሳ ዙሪያ ጥቅምት 25/2014 ዓ/ም የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና ሰጥቷል፡፡ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

በሥልጠናው የጾታና የሥርዓተ-ጾታ ምንነት፣ የጾታዊ ትንኮሳ ዓይነቶች፣ የሴቶች መብት ጥሰት መንገዶችና መፍትሄዎች እና ሥርዓተ-ጾታና የልማት ዕቅዶች ተዳሰዋል፡፡

የዳይሬክቶሬቱ ቡድን መሪ አቶ ዛፉ ዘውዴ እንደገለጹት ሥልጠናው ሴት የአስተዳደር ሠራተኞች በሚሠሩበት ተቋም ውስጥ የሁለቱም ጾታዎች እኩል ተሳታፊነትና ተጠቃሚነትን በማረጋገጥ ጠንካራ የሥራ ባህል እንዲያዳብሩ ለማድረግ ያለመ ነው፡፡ ሴቶች ለራሳቸው የሚሰጡትን ዝቅተኛ ግምት በማስወገድና በራስ መተማመንን በማዳበር ከወንድ አቻዎቻቸው ጋር እኩል ተሳታፊና ተጠቃሚ ሆነው በኑሯቸው ስኬታማ ብሎም ለሀገራቸው አምራች ዜጋ እንዲሆኑ ሥልጠናው እንደሚያግዝም ተናግረዋል፡፡

የዳይሬክቶሬቱ ከፍተኛ ባለሙያ ወ/ሮ ማርሸት ማቴዎስ በበኩላቸው አብዛኛው ማኅበረሰብ በሥርዓተ-ጾታና ጾታ መካከል ያለውን ልዩነት ባለመረዳት ሥርዓተ ጾታ ላይ ያለው አተያይ በተፈጥሮ የተወሰነና የማይለወጥ ውሳኔ አድርጎ መቁጠሩ ሴቶች በውሳኔ ሰጪነት፣ ኢኮኖሚውን በመቆጣጠርና በመሰል ሥራዎች እንዳይሳተፉ አግዷቸዋል፡፡ በመሆኑም መሰል አስተማሪ መድረኮችን በየጊዜው በማዘጋጀት የተሳሳተ አመለካከትና ኢ-ፍትሃዊ የሥርዓተ ጾታ ክፍፍልን በማስቀረት የሀገርን ልማት ለማስቀጠል የበኩላችንን ሚና መወጣት ይጠበቅብናል ሲሉ ባለሙያዋ ተናግረዋል፡፡

ሌላኛው የዳይሬክቶሬቱ ከፍተኛ ባለሙያ አቶ ታደለ ሸዋ የሚፈጠሩት ጾታዊ ትንኮሳዎች እና አካላዊና ሥነ-ልቦናዊ ጥቃቶችን ለማስቀረት በሥርተ-ጾታና በሰብአዊ መብቶች ዙሪያ በቂ ግንዛቤ መፍጠር እንዲሁም ጾታዊ ትንኮሳና ጥቃቶች ሲፈፀሙ ተገቢው ማጣሪያ እንዲደረግና የፍርድ ውሳኔ ማግኘት እንዲቻል ለሚመለከተው የሥራ ክፍል መጠቆም እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡

ሠልጣኞች በሰጡት አስተያየት መድረኩ አስተማሪ ሲሆን መሰል ፕሮግራሞችን በስፋት አዘጋጅቶ ተማሪዎች፣ መምህራንና የአስተዳደር ሠራተኞችን በማሳተፍ ችግሩ እንዳይከሰት አስቀድሞ ግንዛቤ ማስጨበጥ እንዲሁም ጾታዊ ትንኮሳዎች ሲከሰቱ ፍትሃዊ ውሳኔ እንዲያገኙ ጠንክሮ መሥራት ይገባል ብለዋል፡፡