በተፈጥሮና ቀመር ሳይንስ ኮሌጅ (ዓባያ ካምፓስ) የተገነባው የአስተዳደርና የመምህራን ቢሮ ሕንፃ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንትና ሌሎች ከፍተኛና መካከለኛ አመራሮች በተገኙበት ጥቅምት 26/2014 ዓ/ም ተመርቋል፡፡ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የሕንፃው ግንባታ ሥራ በ2010 በጀት ዓመት የተጀመረ ሲሆን ከቢሮዎች ባሻገር የመሰብሰቢያ አዳራሾችን፣ የICT ማዕከላትንና ሌሎች አገልግሎት መስጫ ክፍሎችን ያካተተ ነው፡፡

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ በግንባታው ዘርፍ እንደ ሀገር የሚስተዋሉ ችግሮችን በመቋቋም ይህን መሰል ግዙፍ ሕንፃ በአጭር ጊዜ ውስጥ በማጠናቀቅ ለአገልግሎት እንዲበቃ ላደረጉት ለግንባታ ተቋራጩና አማካሪ ድርጅቱ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡ ሕንፃው ተጠናቆ ሥራ መጀመሩ ለካምፓሱ አስተዳደራዊ ሥራዎች ምቹ ሁኔታ ከመፍጠሩ ባሻገር የመምህራን ቢሮ እጥረትን በመቅረፍ የመማር ማስተማር፣ ምርምርና ሌሎች ሥራዎችን ውጤታማ ከማድረግ አንፃር ጉልህ ሚና ይጫወታል ብለዋል፡፡

የተፈጥሮና ቀመር ሳይንስ ኮሌጅ ዲን ዶ/ር ፈቃዱ ማሴቦ በበኩላቸው የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የቀድሞና የአሁን አመራር አካላት ከካምፓሱ መስፋፋት ጋር ተያይዞ የሚስተዋለውን የመምህራንና የአስተዳደር ሠራተኞች ቢሮ እጥረት ለመቅረፍ ምቹና ዘመናዊ ሕንፃ እንዲሠራ ከመፍቀድ ጀምሮ የግንባታ ሥራው በአጭር ጊዜ ውስጥ እንዲጠናቀቅና ሥራ እንዲጀምር ላደረጉት ድጋፍና ክትትል ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡ የኮሌጁ መምህራንና ሠራተኞች ለዩኒቨርሲቲው ብሎም ለኮሌጁ ሥራ ስኬት በትብብር ሊሠሩ እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡

በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት፣ ም/ፕሬዝደንቶች፣ የኮሌጅ ዲኖች፣ ሳይንቲፊክ ዳይሬክተሮች፣ ዳይሬክተሮችና የካምፓሱ ማኅበረሰብ አባላት ተገኝተዋል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት