Print

የዩኒቨርሲቲው “RUNRES” ፕሮጀክት ከመጀመሪያ ዙር ቆይታው የ2 ዓመታት አፈፃፀሙን ለመቃኘት ኅዳር 02/2014 ዓ/ም በኃይሌ ሪዞርት ወርክሾፕ አዘጋጅቷል፡፡ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የ “RUNRES” ፕሮጀክት ሥራ አስኪያጅ አቶ አባይነህ ፈይሳ እንደገለጹት ፕሮጀክቱ በ4 የአፍሪካ አገሮች ኢትዮጵያ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ሩዋንዳና ኮንጎ ላይ የሚሠራ፣ የ8 ዓመት ቆይታ ያለው እና በ2 ዙር የተከፈለ ሲሆን የመጀመሪያ ዙር ቆይታው ግንቦት/2011 ዓ/ም ፀድቆ ወደ ሥራ ገብቷል፡፡ በፕሮጀክቱ የታቀፉ ኢንተርፕራይዞች ከፕሮጀክቱ ድጋፍ በፊትና በኋላ ያላቸውን አቋም ለመፈተሽ እንዲሁም ከፕሮጀክቱ ጋር በነበራቸው ቆይታ የገጠሟቸውን ችግሮች፣ የደረሱበትን ደረጃና የወደፊት ግባቸውን ለመቃኘት ወርክሾፑ ተዘጋጅቷል፡፡ ይህም የዩኒቨርሲቲው ማኔጅመንት አባላት፣ ተመራማሪዎች እና የዞን፣ የከተማና የቀበሌ መዋቅር ላይ ያሉ አካላት አፈፃፀሙን ከኢንተርፕራይዞቹ በቀጥታ እንዲረዱ የሚያደርግ ሲሆን ለተመራማሪዎችም የምርምር ሃሳብ የሚያቀብል ነው ብለዋል፡፡

እንደ አቶ አባይነህ ገለጻ ባለፉት 2 ዓመታት በፕሮጀክቱ በአርባ ምንጭ ከተማና አካባቢዋ በተለዩ ሦስት የትኩረት መስኮች፡- በግብርና ማቀነባበሪያ፣ ማዘጋጃ ቤታዊ ደረቅ ቆሻሻን ኮምፖስት አድርጎ መመለስና ከሰው ሽንት ማዳበሪያ ማዘጋጀት ላይ ቴክኖሎጂዎቹ ከአካባቢው ነባራዊ ሁኔታ ጋር የሚስማሙ ስለመሆናቸው፣ የምርቶቹን ማኅበራዊ ቅቡልነት እንዲሁም ኢኮኖሚያዊ አዋጭነታቸው ላይ የዳሰሳ ጥናት ተደርጓል፡፡ በዚህም መሠረት የቢዝነስ ዕቅድ ያቀረቡ ኢንተርፕራይዞች ተወዳድረው ከፕሮጀክቱ ጋር ሥራ ጀምረዋል፡፡

በወርክሾፑ ‹‹እኛን ነው ማየት ቀልዝ ሥራ ማኅበር››፣ ‹‹አንጆ ኑስ የአትክልትና ፍራፍሬ ማቀነባበሪያ ኢንተርፕራይዝ›› እና ‹‹MASSP Human Urine Recycling Group›› ከፕሮጀክቱ ጋር ባላቸው የ2 ዓመታት ቆይታ የገጠሟቸውን ችግሮች፣ የመፍትሔ ሃሳቦችና መልካም አጋጣሚዎችን ያቀረቡ ሲሆን በመሥሪያ ቦታቸው በመገኘት የመስክ ጉብኝትም ተካሂዷል፡፡ ኢንተርፕራይዞቹ ጥሬ ሙዝን አድርቆ በመፍጨት የሙዝ ዱቄትን ለተለያዩ አገልግሎቶች የሚያቀርቡ፣ በከተማው ከየሰው ቤት የተሰበሰበውን ቆሻሻ በመለየት የተፈጥሮ ማዳበሪያ የሚያዘጋጁና የሰው ሽንትን ወደ ማዳበሪያ የሚቀይሩ ናቸው፡፡ የማኅበረሰቡ ግንዛቤ እጥረት፣ በኮቪድ - 19 ወረርሽኝ ምክንያት የክፍያ መዘግየት፣ የማስታወቂያና ገበያ ትስስር ማነስ፣ ወደ ገበያ ለመውጣት የጥራት ደረጃ ማረጋገጫ ሂደቶች መዘግየት፣ የቆሻሻ ማጓጓዣ ተሽከርካሪና የዘመናዊ ማሽኖች አለመኖር እና ከመንግሥት አካላት በቂ ትኩረትና ድጋፍ ማጣት ከተነሱ ችግሮች መካከል ይጠቀሳሉ፡፡ የግንዛቤ ክፍተትና የገበያ ትስስር ችግሮች በሂደት የሚቀረፉ መሆኑ የተጠቀሰ ሲሆን የቆሻሻ ማጓጓዣ ተሽከርካሪና የዘመናዊ ማሽኖች ግዢ በሂደት ላይ መሆናቸው ተገልጿል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ከዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር በትብብር ከሚመራቸው ፕሮጀክቶች አንዱ “RUNRES” መሆኑን ገልጸው ምርትና ተረፈ ምርትን አዟዙሮ በመጠቀም በአርሶ አደሩና በከተማው ማኅበረሰብ መካከል ትስስርን የሚፈጥርና ዩኒቨርሲቲው በግብርናው ዘርፍ ለሚያከናውናቸው ዘርፈ ብዙ ተግባራት በጎ ተፅዕኖ የሚያሳድር መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የማኅበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተርና የምርምርና ማ/አገ/ም/ፕሬዝደንት ተወካይ ዶ/ር ተክሉ ወጋየሁ በበኩላቸው ምርምር ማዕከላዊ ተልዕኮው የሆነው አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ቀጣይ ትኩረቱ ምርምር መር የሆነ የመማር

ማስተማር ሥርዓትና የማኅበረሰብ አገልግሎት መሆኑን ጠቅሰው “RUNRES” ፕሮጀክትም በቆይታው ለዚህ ተልዕኮ ጉልህ ሚና ይኖረዋል ብለዋል፡፡

የአካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር ዓለማየሁ ጩፋሞ በመዝጊያ ንግግራቸው በወርክሾፑ በቀረበው የፕሮጀክቱና የኢንተርፕራይዞች አፈፃፀም እንዲሁም በመስክ ጉብኝቱ ወቅት ባዩት ነገር መደሰታቸውን ገልጸዋል፡፡ ኢንተርፕራይዞቹ በበርካታ ተግዳሮቶች ውስጥ አልፈው አዳዲስና ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊና የጤና ፋይዳ ያላቸውን ሃሳቦች ተግባር ላይ ማዋላቸው የሚበረታታና ቀጣይነት ያለው ድጋፍ የሚሻ ነው ብለዋል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት