Print

የዩኒቨርሲቲው የማኅበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት በጋሞ ዞን ጋጮ ባባ ወረዳ ለሚገነባው ድልድይ ኅዳር 16/2014 ዓ/ም የዲዛይን ግምገማ አካሂዷል፡፡ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ሳይንቲፊክ ዳይሬክተር ዶ/ር ሙሉነህ ለማ ዩኒቨርሲቲው በምርምርና በማኅበረሰብ አገልግሎት ዘርፍ በይበልጥ መሥራት እንደሚጠበቅበት ጠቅሰው ከጋሞ ዞን ጋር በጋራ ለመሥራት የመግባቢያ ሰነዶችን በመፈራረምና ዕቅድ በማዘጋጀት ወደፊትም በርካታ ሥራዎችን እንሠራለን ብለዋል፡፡

የልማት ሥራዎች ማስተባበሪያ ጽ/ቤት አስተባባሪ ረ/ፕ ይበልጣል ይሁኔ በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው የልማት ሥራዎችን ከዞንና ከወረዳዎች ጋር በጋራ እንደሚሠራ ተናግረው በጋጮ ባባ ወረዳ ለሚገነባው ድልድይ ዲዛይን እንዲሠራ በ2010 ዓ/ም ወረዳው በጠየቀው መሠረት ዲዛይኑ መዘጋጀቱን ገልጸዋል፡፡

የሲቪል ምኅንድስና ፋከልቲ ዲን አቶ ሀብታሙ መለሰ እንደገለጹት በወረዳው ቀድሞ የነበረው ድልድይ በመፍረሱ ምክንያት ማኅበረሰቡ ት/ቤት ለመሄድ፣ በጤና ተቋማት ሕክምና ለማግኘት፣ አርሶ አደሩ ምርቱን ወደ ገበያ ለማድረስና ሌሎችም ችግሮችን አስከትሏል፡፡ ወረዳው ችግሩን ለመቅረፍ ሲዘጋጅ ዩኒቨርሲቲው በሙያ ማገዝ ስላለበት የድልድይ ዲዛይኑን አዘጋጅቶ ግምገማ አድርጓል ብለዋል፡፡

በጋሞ ዞን መንገድና ትራንስፖርት ልማት መምሪያ የትራንስፖርት ዘርፍ ኃላፊ ወ/ሮ መሳይ ጌታቸው እንደገለጹት ጥናቱ ከተጀመረ ረጅም ጊዜ ያስቆጠረ ሲሆን በ2014 ዓ/ም በጋሞ ዞን አስተዳደር በጀት ተይዞለታል፡፡ በዲዛይኑ ግምገማ ዲዛይኑ ወደ ግንባታ ከመግባቱ በፊት የዲዛይኑን ሕዝባዊ ተቀባይነትና ሌሎች ጉዳዮችንም ማየታቸውን ወ/ሮ መሳይ ተናግረዋል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት