Print

በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ለሚያስተምሩ ነባር የሕክምና መምህራን ‹‹Case Based Discussion›› በተሰኘ የሕክምና ትምህርት ማስተማሪያና የምዘና ዘዴ ላይ ከኅዳር 27 - ታኅሳስ 1/2014 ዓ/ም ለ5 ተከታታይ ቀናት ሥልጠና ተሰጥቷል፡፡ የኬዝ አፃፃፍ ዘዴዎች እና ኬዞችን ተጠቅሞ ተማሪዎችን ማስተማርና መመዘን የሥልጠናው የትኩረት ነጥቦች ናቸው፡፡ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የሥልጠናው አስተባባሪ ዕጩ ዶ/ር እኩልነት ምሥጋናው እንደገለጹት ሥልጠናው ጀርመን ሀገር ከሚገኘው LMU ከተሰኘ የሕክምና ዩኒቨርሲቲ በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ የተሰጠ ሲሆን በሥልጠናው 20 የኮሌጁ መምህራን ተሳትፈዋል፡፡ የዚሁ ፕሮጀክት አካል የሆነ መሰል ሥልጠና ‹‹Problem Based Learning›› በሚል ርዕስ በጂማ ዩኒቨርሲቲ የሕክምና መምህራን መሰጠቱን የጠቀሱት አስተባባሪው ሥልጠናው የተሰጠባቸው የማስተማሪያና የመገምገሚያ ሥነ-ዘዴዎች የሕክምና ትምህርት አሰጣጥን በማሻሻል ብቁና ጥራት ያላቸው የሕክምና ዶክተሮችን ለማፍራት ያግዛሉ ብለዋል፡፡

በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የሕክምና ት/ቤት የውስጥ ደዌ ሐኪምና አሠልጣኝ ዶ/ር ታዲዮስ ኃይሉ በበኩላቸው እንደ ኮሌጅ የሕክምና ትምህርት አሠጣጥ ሂደቱን ለማሻሻል በርካታ ሥራዎች እንደሚሠሩ ተናግረው ይህም ሥልጠና የዚሁ ሥራ አካል ነው ብለዋል፡፡ ‹‹Case Based Discussion›› የተሰኘው የሕክምና ትምህርት የማስተማሪያ ዘዴ የትምህርት አሰጣጡን በደንብ በተረቀቁ ኬዞች ላይ ተመሥርቶ የሚሰጥ ሲሆን ይህም ዘዴ በተለያዩ ዓለም አቀፍ የሕክምና ት/ቤቶች ተሞክሮ ውጤታማነቱ የተረጋገጠ ነው፡፡ ዘዴው ተማሪዎች ኬዞችን ተንትነው በተለያየ አቅጣጫ እንዲመለከቱ ያደርጋል ያሉት አሠልጣኙ በተለይ የተማሪዎቹን በሕክምና ትምህርትና ሥራ ውስጥ ወሳኝ የሆነውን ‹‹Clinical Reasoning Skill›› በማጎልበት ረገድ ጉልህ ሚና እንደሚጫወት ጠቁመዋል፡፡ ከዚህ ቀደም የተለያዩ መምህራን ባልተደራጀና መደበኛ ባልሆነ መንገድ ይህንን ዘዴ ሲጠቀሙ ይታያል ያሉት ዶ/ር ታዲዮስ ከዚህ በኋላ ግን ዘዴው በተደራጀና መደበኛ በሆነ መንገድ አንዱ የማስተማሪያና ምዘና ዘዴ ሆኖ በኮሌጁ ተግባራዊ ይደረጋል ብለዋል፡፡

ከሥልጠናው ተሳታፊ መምህራን መካከል ዶ/ር ዓለማየሁ ሻንቆ ከዚህ ቀደም ይህንን ዘዴ በተወሰነ ደረጃ ለማስተማር ይጠቀሙ እንደነበር አስታውሰው ሥልጠናው ዘዴውን በተደራጀ መንገድ ለመጠቀም የሚያግዝ ነው ብለዋል፡፡ ከዚህም ባሸገር ዘዴው የተማሪዎቹን ለውጥ በየጊዜው ለመገምገም እንደሚያግዝ ከሥልጠው ግንዛቤ ማግኝታቸውንም ተናግረዋል፡፡

ከሥልጠናው አስተባባሪዎች የተገኘው መረጃ እንደሚጠቁመው በሥልጠናው ሂደት ለዚሁ ዘዴ ማስተማሪያነት የሚረዱ 36 ኬዞች ተተንትነው የተጻፉ ሲሆን ኬዞቹ በተለያዩ አካላት አስተያየት ከተሰጠባቸውና ማሻሻያዎች ከተደረጉባቸው በኋላ ታትመው ለማስተማሪያነት ያገለግላሉ፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት