Print

በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በሕግ ሲታዩ የቆዩ የግድያ፣ የአስገድዶ መድፈር እና የአዳራሽ ወንበር ግዢ ክሶች የፍ/ቤት ውሳኔ የተሰጠባቸው መሆኑ ታኅሣሥ 13/2014 ዓ.ም በዩኒቨርሲቲው የሕግ አገልግሎት ዳይሬክተር ተገልጿል፡፡

የዩኒቨርሲቲው የሕግ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ መርኪያ መንገሻ እንደገለጹት በአርባ ምንጭ ከተማ ኩልፎ ወንዝ ዳርቻ ሞተው የተገኙት የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ መምህር አቶ ዋቁማ ተስፋዬን ጉዳይ ፖሊስ ጥብቅ ክትትል ሲያደርግ ቆይቶ ገዳዮቹን ለፍርድ ማቅረብ ተችሏል፡፡ ሟች ለግል ጉዳያቸው ከሄዱበት ሲመለሱ ባለ ሦስት እግር ተሽከርካሪ ተጠቅመው ወደ አሳቻ ስፍራ በመሰወርና ድብደባ በመፈፀም ሕይወታቸው እንዲያልፍ መደረጉን በሐኪምና ሌሎች ፖሊሳዊ ማስረጃዎች መረጋገጡን አቶ መርኪያ ገልጸዋል፡፡ ወንጀሉ ሆነ ተብሎ በቡድን የተቀነባበረና የተፈጸመ መሆኑን የጠቀሰው የጋሞ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ኅዳር 29/2014 ዓ.ም በዋለው ችሎት ወንጀለኞች በ14 ዓመት ጽኑ እስራት እንዲቀጡ ፍርድ ሰጥቷል ሲሉ አቶ መርኪያ ተናግረዋል፡፡

አቶ መርኪያ እንደተናገሩት መስከረም 30/2014 ዓ.ም በሳውላ ካምፓስ ተመራቂ ተማሪ የነበረችውን ተበዳይ ወደ ካምፓሷ በመመለስ ላይ እያለች የመድፈር ወንጀል የፈፀሙ የባለ 3 እግር ተሽከርካሪ ሹፌርና ግብረ አበሩ በካምፓሱ ጥበቃ፣ በመኝታ አገልግሎት፣ በፖሊስና ደኅንነት ሠራተኞች፣ በሴቶች፣ ሕፃናትና ወጣቶች ጉዳይ እና በሕግ አገልግሎት ዳይሬክቶሬቶች ትብብር ጉዳዩ ለሕግ እንዲቀርብ ተደርጓል፡፡ የሳውላ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ተማሪዋ መደፈሯን በማረጋገጥ በጥፋተኞቹ ላይ የ5 ዓመት እስራት ውሳኔ ያስተላለፈ ቢሆንም ወንጀሉን የያዘው አቃቤ ሕግ ፍርዱ ተመጣጣኝ ባለመሆኑ ይግባኝ በመጠየቅ ኅዳር 29/2014 ዓ.ም የጎፋ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት በዋለው ችሎት በጥፋተኞቹ ላይ የ11 ዓመት ጽኑ እስራት ፍርድ መሰጠቱን አቶ መርኪያ ተናግረዋል፡፡

ሌላው የክስ ጉዳይ የአዳራሽ ወንበር ግዥ ነው ያሉት አቶ መርኪያ ‹‹ዋው ፕራይም ሃውስ ፈርኒቸር ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር›› ለዩኒቨርሲቲው ያቀረባቸው ወንበሮች ጥራቱን ያላሟሉና ልዩነት ያሳዩ በመሆኑ በጥራት አረጋጋጭ ኮሚቴ ተጣርቶ በተቀባይ መሥሪያ ቤቱ ተቀባይነትን ሳያገኝ መቅረቱን ተናግረዋል፡፡

በወንበሮቹ ላይ እንደ ችግር የቀረቡት ጉዳዮች የወንበሩ ልኬት 60 ሴ.ሜ መሆን ሲገባው የቀረበው 56.58 ሴ.ሜ መሆኑ፣ የጎን መደገፊያ PVC መሆን ሲገባው በቀላሉ በውሃ ሊሰባበር የሚችል ቺፑድ መደረጉ እና ለመጻፊያነት የተመረጠው በቀላሉ ሊተጣጠፍ የሚችል መሆን ሲገባው የማይተጣጠፍ መሆኑ፣ የጀርባ መደገፊያው PVC መሆን ሲገባው ቺፑድ መደረጉ ከዋና ዋና የግዢ መስፈርት ጉድለቶች መካከል መሆናቸውን አቶ መርኪያ ገልጸዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው ጥራት አሟልቶ ላልቀረበ ግዢ ክፍያ መፈፀም የማይችል መሆኑን በደብዳቤ ያሳወቀ ሲሆን በዚህም መነሻነት ድርጅቱ በዩኒቨርሲቲው ላይ በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመዝገብ ቁጥር 2207162 ክስ መሥርቷል፡፡ አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲም ድርጅቱ ክስ መመሥረቱን ባለማወቅ በመዝገብ ቁጥር 220800 ክስ በመክፈት ድርጅቱ የወሰደውን ቅድመ ክፍያ እንዲመልስ የጠየቀ ሲሆን ጉዳዩ በከፍተኛ ፍርድ ቤት ተጣምሮ እንዲታይ በይኖ ሲታይ ቆይቷል፡፡

አቶ መርኪያ መዝገቡን የመረመረው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልዩነት ተብለው የቀረቡት ጉዳዮች ዓይነተኛ ልዩነቶች ባለመሆናቸው ዩኒቨርሲቲው ወንበሩን በመረከብ ቀሪውን ክፍያ ከሰኔ/2010 ዓ/ም ጀምሮ ከወለድ ጋር እንዲከፍል ወስኗል

ብለዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው በውሳኔው ላይ ቅሬታ በማሰማት ይግባኝ ለፌዴራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ያቀረበ በመሆኑ ይግባኙን ሲመረምር የቆው ጠቅላይ ፍ/ቤት የከፍተኛ ፍ/ቤት ውሳኔ ሙሉ በሙሉ ተሽሮ መዝገቡ ወደ ከፍተኛ ፍ/ቤት ተመልሶ እንደገና እንዲመረመርና ልዩነቱ በገለልተኛ አካል ተጠንቶ እንዲቀርብ ውሳኔ ተላልፎ ሂደት ላይ መሆኑን አቶ መርኪያ ገልጸዋል፡፡

በዩኒቨርሲቲው ጥቅምና ገጽታ ግንባታ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ የፈጠሩ የኢሳት ቴሌቪዢን፣ የማኅበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚ ግለሰቦች፣ የውል ግዴታዎቻቸውን ባልተወጡ መምህራን ላይ የተመሠረቱ ክሶችና ሌሎችም በዩኒቨርሲቲው በሕግ ተይዘው እየታዩ ከሚገኙ ጉዳዮች መካከል ይገኛሉ፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት