Print

የአገሪቱን መረጃና የመረጃ መሠረተ ልማቶች ለመጠበቅ የሚያስችል አቅም በመገንባት የኢትዮጵያን ብሄራዊ ጥቅም የማስጠበቅ ተልዕኮን አንግቦ እየሠራ የሚገኘው የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት ኤጀንሲ /INSA/ ከአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመስኩ የሠለጠነ የሰው ኃይል ለማፍራት እንዲሁም በምርምርና ልማት ሥራዎች ላይ በትብብር ለመሥራት በሚያስችሉ ጉዳዮች ዙሪያ የካቲት 10/2014 ዓ/ም ውይይት አካሂዷል፡፡ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ አካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዝደንትና የፕሬዝደንቱ ተወካይ ዶ/ር ዓለማየሁ ጩፋሞ አገራችን ያለችበት ጂኦፖለቲካዊ ሁኔታ በተለይ ከዓባይ ወንዝና ሕዳሴ ግድብ ጋር ተያይዞ ያለው ጫናና ተጽዕኖን ለመቋቋም በሁሉም መስክ እራሳችንን በተገቢው ሁኔታ ማዘጋጀት ይጠበቅብናል ብለዋል፡፡

በተደጋጋሚ ከኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት ኤጀንሲ የሚወጡ መረጃዎች በሀገራችን ላይ የሚደርሱ የሳይበር ጥቃቶች እየጨመሩ መምጣታቸውን ያመላክታል ያሉት ዶ/ር ዓለማየሁ ይህንን ጥቃት ለመመከትና ለቀጣይ አስተማማኝ የሳይበር ምኅዳር ለመፍጠር ልዩ ተሰጥኦ ያላቸውን የመስኩ ተማሪዎችንና ባለሙያዎችን በማስተማርና በማንቃት ከወዲሁ እንዲዘጋጁና ተገቢ ዕውቀት እንዲታጠቁ ማድረግ የህልውና ጉዳይ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡ በዚህ ረገድ ኤጀንሲው ቅድሚያውን ወስዶ አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲን ጨምሮ ከምርምር ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በጋራ ለመሥራት ማሰቡና እንቅስቃሴ መጀመሩ ወቅቱ የሚፈልገው አገራዊ ዕይታና ምላሽ ነውም ብለዋል፡፡

በኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት ኤጀንሲ የሳይበር ደኅንነት ማኔጅመንት ክፍል ኃላፊ አቶ ፍጹም ወሰኔ በበኩላቸው የሳይበር ቴክኖሎጂ ድንበር የለሽ፣ ዓለም አቀፍ፣ ምናባዊ፣ ያልተማከለና ለቁጥጥር አዳጋች መሆኑን ጠቅሰው በሀክቲቪስቶች፣ በውስጥና በተሰናበቱ ሠራተኞች፣ በመንግሥታት፣ በቴክኖሎጂ ድርጅቶችና በተደራጁ ወንጀለኞች አማካኝነት በአገራት የሳይበር መሠረተ ልማቶች ላይ ጥቃቶች እንደሚፈጸሙ ጠቁመዋል፡፡ በአገራችን ላይ የሚሞከሩ የሳይበር ጥቃቶች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመሩ መምጣታቸውን የተናገሩት ኃላፊው በ2013 ዓ/ም 2,800 ጥቃቶች እንዲሁም በ2014 ዓ/ም ግማሽ ዓመት ብቻ 3,406 ጥቃቶች እንደተሞከሩ ገልጸዋል፡፡

በአገራችን የሚገኙ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በአገራዊ የሳይበር ደኅንነት አቅም ግንባታ ላይ ተገቢውን ሚና እንዲጫወቱ ለማስቻል ኤጀንሲው ከዩኒቨርሲቲዎች ጋር የሳይበር ደኅንነት ምርምር ማዕከላትንና ማኅበራትን በጋራ ማቋቋምና ማደራጀት፣ በጋራ የሚሠሩ የምርምርና ልማት ፕሮጀክቶችን መንደፍና መሥራት፣ የተለያዩ የሳይበር ደኅንነት ምርምርና ዕውቀት ሽግግር መድረኮችን ማመቻቸትና ማዘጋጀት እንዲሁም በትምህርት ሥርዓት ውስጥ ዘርፉን ሊያሳድጉ የሚችሉ የትምህርት ኮርሶችንና ሥርዓተ-ትምህርቶችን ማዘጋጀት ላይ በትብብር ለመሥራት ማቀዱን ተናግረዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲዎችም በዘርፉ ብቁ የሰው ኃይል ማፍሪያ፣ የሳይበር ደኅንነት ጥናትና ምርምር ማዕከል መሆንና የሳይበር ደኅንነት ማስጠበቂያ ቴክኖሎጂዎች መፍለቂያ እንዲሆኑ ይጠበቃል ብለዋል፡፡

በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የኢንዱስትሪ ትስስርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ቶሌራ ሴዳ ዩኒቨርሲቲው ከተለያዩ አምራች ኢንደስትሪዎች እና ጋርና መንግሥታዊና መንግሥታዊ ካልሆኑ ዓለም አቀፍ፣ የክልልና የፌዴራል መሥሪያ ቤቶችና ተቋማት ጋር የመግባቢያ ስምምነቶችን በመፈራረም በትብብር እየሠራ መሆኑን ጠቁመው

ዩኒቨርሲቲው ከኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት ኤጀንሲ ጋርም በሳይበር ደህንነት ዘርፍ ላይ በጥናትና ምርምርም ሆነ በመስኩ የሰው ሃይል በማፍራት ረገድ በትብብር ለመሥራት ዝግጁ ነው ብለዋል፡፡

የአርባ ምንጭ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ሳይንቲፊክ ዳይሬክተር ዶ/ር ሙሉነህ ለማ በበኩላቸው ኢንስቲትዩቱ ከዘርፉ ጋር ተያያዥነት ያላቸው ከመጀመሪያ ዲግሪ እስከ 3ኛ ዲግሪ ያሉ የትምህርት ፕሮግራሞችን ቀርጾ ከኤጀንሲው ጋር በመስኩ ለመሥራት የሚያስችሉ የተደራጁ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ወርክሾፖችና ቤተ-ሙከራዎች መኖራቸውንም ጠቁመዋል፡፡ ከዚህም ባሻገር ኢንስቲትዩቱ በቅርቡ በኔትወርክ ደኅንነት /NETWORK SECURITY/ አዲስ የ2ኛ ዲግሪ ፕሮግራም ለመክፈት ዝግጅት እያደረገ መሆኑን የጠቆሙት ዶ/ር ሙሉነህ ያለን የሰው ኃይልና መሠረተ ልማት ኤጀንሲው ጋር በሁሉም መስክ በትብብር ለመሥራት የሚያስችል ነው ብለዋል፡፡

በውይይት መድረኩ ላይ የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛና መካከለኛ አመራሮች፣ የመስኩ መምህራንና የICT ባለሙያዎችና የ2ኛ የ3ኛ ዲግሪ ተማሪዎች የተሳተፉ ሲሆን ከኤጀንሲው የመጣው የልዑካን ቡድን ከውይይቱ ባሻገር ዩኒቨርሲቲው በመስኩ ያለውን አቅም ለመገምገም በማለም በዩኒቨርሲቲው ዋናው ግቢ፣ ዓባያና ጫሞ ካምፓስ የሚገኙ ቤተ-ሙከራዎችንና የICT መሠረተ ልማቶችን ጎብኝቷል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት