Print

የዩኒቨርሲቲው ሴቶች፣ ሕፃናትና ወጣቶች ጉዳይ ዳይሬክቶሬት ከሰው ሀብት ልማትና አስተዳደር ዳይሬክቶሬት፣ ከለውጥና መልካም አስተዳደር ዳይሬክቶሬት እና ከማኔጅመንት ት/ክፍል ጋር በመተባበር ከተለያዩ የሥራ ክፍሎች ለተወጣጡ አገልግሎት ሰጪ ሠራተኞች በደንበኛ አያያዝና ጥራት ያለው አገልግሎት አሰጣጥ ዙሪያ ከየካቲት 10-11/2014 ዓ/ም ሥልጠና ሰጥቷል፡፡ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የለውጥ መሳሪያዎች ትስስር፣ የመንግሥት ሥራ ምንነት፣ የደንበኛ ምንነትና አያያዝ የሚሉ ርዕሰ ጉዳዮች የሥልጠናው የትኩረት ነጥቦች ነበሩ፡፡
የፕሬዝደንት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ገዝሙ ቀልቦ በመክፈቻ ንግግራቸው ዕቅድን ለማሳካት የሰው ኃይልን በአቅም መገንባት ትልቅ ሚና ያለው መሆኑን ጠቁመው የዚህ ዓይነት ሥልጠናዎች የተቋም ዕቅድንና ተልዕኮን ከመፈፀም አንፃር አቅምና መነሳሳት የሚፈጥሩ ናቸው ብለዋል፡፡ ሠልጣኞች በተለያየ መንገድ ራሳቸውን በዕውቀት በመገንባት ያላቸውን ዕምቅ ኃይል ተግባር ላይ በማዋል ለጥሩ ውጤት ሊሠሩ እንደሚገባ አቶ ገዝሙ አስገንዝበዋል፡፡

የለውጥና መልካም አስተዳደር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተርና አሠልጣኝ አቶ በኃይሉ በፈቃዱ በበኩላቸው ሠልጣኞች የለውጥ ምንነትንና ጠቀሜታን ተረድተው ከነበረው ልማዳዊ የአሠራር ዘይቤ ወደ አዲስ ሁለንተናዊ አስተሳሰብና ተግባር የሚሻገሩበት ዕድል ከሥልጠናው እንደሚያገኙ ተናግረዋል፡፡ ሥልጠናው ሠራተኞች ሥራቸውን በሚያከናውኑ ወቅት ዕቅድን መሠረት በማድረግ እንዲሠሩ ከማስቻሉ ባሻገር ሥራዎችን ጊዜና ጥራትን የጠበቀ በማድረግ ቀጣይነት ያለው ለውጥ ለማምጣት ያግዛል ብለዋል፡፡

የሰው ሀብት ልማትና አስተዳደር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተርና አሠልጣኝ ወ/ሮ ከአምላክነሽ ደሳለኝ ሥልጠናው ሠራተኞች የመንግሥት ሥራን ምንነት በመረዳት ለሚሰጡት አገልግሎት ንቃትን በመፍጠር አመርቂ ውጤት ማምጣት እንዲችሉ እንደሚረዳ ተናግረዋል፡፡ የዩኒቨርሲቲው ግብ የበቁ ምሩቃንን ማፍራት በመሆኑ ተቋሙ የተቋቋመበትን ዓላማ ጠንቅቀው በመረዳት ሥራቸውን እንዲያከናውኑም ሥልጠናው አጋዥ ነው ብለዋል፡፡

የማኔጅመንት ት/ክፍል መምህርትና አሠልጣኝ ውዴ መንግሥቱ በበኩላቸው የተቋሙ ዋና ዓላማ ጥራት ያለው ትምህርት መስጠት መሆኑን አስታውሰው ሥልጠናው በዩኒቨርሲቲው ሥር ያሉ ሠራተኞች አገልግሎት ፈላጊ ደንበኞች ምን እንደሚፈልጉና እንዴት መስተናገድ እንዳለባቸው የሚያዩበትና ለሥራቸው አጋዥ መነሻ ሃሳቦችን የሚጨብጡበት መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ሠልጣኞች በሰጡት አስተያየት ሥልጠናው አነቃቂና ከዚህ በፊት የማያውቋቸውን ጠቃሚ ጽንሰ ሃሳቦች ያወቁበት መሆኑን ተናግረው ይህም ቀጣይ የሥራ አፈፃፀማቸውን ከፍ እንደሚያደርግ ጠቁመዋል፡፡
የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት