Print

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሰቲ የምር/ማኅ/አገ/ም/ፕ/ጽ/ቤት ከ‹‹አገልግል የተፈጥሮ ልማትና ጥበቃ የበጎ አድራጎት ማኅበር›› ጋር በመተባበር ‹‹ወጣትነት፣ ህልምና ሀገራዊ አንድነት›› በሚል መሪ ቃል ለዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች ከመጋቢት 5-6/2014 ዓ/ም የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ አዘጋጅቷል፡፡ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የምርምርና ማኅበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዝደንት ተ/ፕ በኃይሉ መርደኪዮስ ወጣትነት ተሩጦ የማይጠገብበትና ብዙ መልካም ዕድሎችን የያዘ የእድሜ ክልል ሲሆን በጥንቃቄና በማስተዋል ካልተጓዝን ውድቀቱ የከፋ የሚሆንበትና በጥሩ ጎኑ ከተረዳነው እንዲሁም የብዙ ህልም ባለቤት የሚኮንበትና ከራስ አልፎ ለሌሎች የሚተርፍ ትልቅ ሥራ የሚሠራበት ጊዜ ነው ብለዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ በድሩ ሂሪጎ ወጣቱ በአሁኑ ሰዓት በሀገራች የሚስተዋሉትን የተለያዩ ችግሮች ለመፍታት አቅምና ዕድሉ ያለው በመሆኑ በጎና ጠቃሚ ሃሳቦችን በመቀበልና በጥናትና ምርምር በማጠናከር ለወገኑም ሆነ ለሀገሩ ቀጣዩ ትውልድ የሚኮራበትን ታሪክ ሊሠራ ይገባል ብለዋል፡፡ ሀገራችን ባለችበት ወቅታዊ ሁኔታ የተሳሳቱ መረጃዎች ስርጭት ኅብረተሰቡን እየረበሸ የሚገኝ መሆኑን የጠቀሱት ዳይሬክተሩ ወጣቱ በበጎነትና በአገልጋይነት መንፈስ የሐሰተኛ መረጃዎችን ስርጭት በመግታት የወገኑና የሀገሩ ዘብ የመሆን ኃላፊነቱን እንዳይዘነጋ አሳስበዋል፡፡ እንደ ተቋም አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በቀጣይም አሸናፊና ገንቢ ሃሳቦች የሚንሸራሸሩበትና ተማሪዎች ስለሀገራችንም ሆነ ስለ አጠቃላይ ዓለም መልካም ተሞክሮዎችን በመቀመር የተሻለ ግንዛቤ የሚጨብጡባቸውን መሰል መድረኮች በማዘጋጀት ለሀገር የሚጠቅሙ ዜጋ እንዲሆኑ ጠንክሮ የሚሠራ መሆኑን አቶ በድሩ ገልጸዋል፡፡

‹‹ወንድማማችነት፣ ኅብረ-ብሄራዊነትና በጎነት›› በሚል ርዕስ የውይይት ሰነድ ያቀረቡት የዩኒቨርሲቲው የባህልና ቋንቋ ጥናት ኢንስቲትዩት ዳይሬክተር ዶ/ር ሰኢድ አሕመድ በጎነት ፈልገን እንጂ አድርጉ ተብለን ታዘን የምንፈጽመው ተግባር ባለመሆኑ ከግለሰብ ጀምሮ መሰጠትን የሚጠይቅና ማኅበራዊ ፋይዳውም የጎላ በመሆኑ በትኩረት ልንሠራበት እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡ ዶ/ር ሰኢድ አክለውም ወጣቱ ከጥገኝነት ስሜት ተላቆና ያለውን አቅም ተጠቅሞ ከሀገር ጠባቂ ሳይሆን ለሀገር ጠቃሚ ሥራ ሠርቶ ባለታሪክ ሆኖ ለማለፍ ራዕይ አንግቦ እንዲተጋ አሳስበዋል፡፡ እንደ ሀገር የተመዘገቡት እንደ አድዋ ድል ያሉና ሌሎችም ትልልቅ ድሎች እንዲመዘገቡ የኢትዮጵያ ሕዝብ በወንድማማችነት መደጋገፉ፣ ሀገራዊ አንድነቱን መጠበቁና በበጎነትና ቅንነት መታገሉ ፋይዳው የጎላ መሆኑንም ዶ/ር ሰኢድ ከታሪክ አንጻር ቃኝተዋል፡፡

የ‹‹አገልግል የተፈጥሮ ልማትና ጥበቃ የበጎ አድራጎት ማኅበር›› መሥራች አቶ ታደሰ ልብሴ በበኩሉ ወጣት ተማሪዎች ጊዜያቸውን በአግባቡ እንዲመሩ ለማስቻል፣ ከሚዲያ ተጽዕኖና ከእኩይ ተግባሮች ራሳቸውን ማዳን እንዳለባቸው ለማስገንዘብ መድረኩ ተዘጋጅቷል ብሏል፡፡ እንደ አቶ ታደሰ ገለጻ ወጣቱ ትልቅ ህልምና ዕድል ያለው በመሆኑ ምንም ዓይነት ተስፋ አስቆራጭ ክስተቶች ቢገጥሙትም እንኳን በመረዳዳትና በጽናት ማለፍ እንደሚቻል ጥልቅ ግንዛቤን በመፍጠር በወንድማማችነት እሴት ላይ የራሱን አሻራ ማሳረፍ እንዲችልና በተፈጥሮ ልማትና ጥበቃ ላይ በትኩረት

የመሥራት ባህልን እንዲያዳብር ማድረግ ይገባል፡፡ ተማሪዎች መሰል ፕሮግራሞችን በመሳተፍ የሕይወት መስመራቸውን ስኬታማ ማድረግ የሚችሉ መሆኑን አቶ ታደሰ ጠቁሟል፡፡

የዕለቱ ተጋባዥ እንግዳ ወ/ሮ ባንቺአምላክ አዲሱ እንደ ሀገር የቱሪዝም፣ የተፈጥሮና የባህል ሀብቶቻችን ላይ በበቂ ሁኔታ ያልተሠራ በመሆኑ ወደ ኢንደስትሪና ኢኮኖሚ ያልተለወጡ በርካታ ሥራዎች ያሉ በመሆኑ ከወጣቱ ብዙ ይጠበቃል ብለዋል፡፡ የተቋሙን ወጣት ባለራዕይ ማድረግ ከዩኒቨርሲቲውም ሆነ ሌሎች ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የሚጠበቅ በመሆኑ መሰል ፕሮግራሞች የአንድ ጊዜ ኩነት ብቻ ሳይሆኑ ተከታታይነት ቢኖራቸው የአስተሳሰብ አድማስን ለማጎልበት እንደሚረዱ ተናግረዋል፡፡

በመድረኩ አነቃቂ ንግግሮች፣ የተለያዩ ኪነ-ጥበባዊ ሥራዎች፣ በወንድማማችነት፣ በሀገራዊ አንድነትና የበጎ አድራጎት አስፈላጊነት ዙሪያ ያተኮረ የውይይት ሰነድ እንዲሁም የስኬታማ ወጣቶች የሕይወት ተሞክሮ ቀርቧል፡፡ ተጓዡ ጋዜጠኛ ሄኖክ ሥዩምና የሁራ ሚዲያ ፕላስ መሥራች አቶ ሄኖክ ተስፋዬ የወጣቱ ባለራዕይ መሆን ካሳበበት ግብ ለመድረስ ያለውን አስተዋጽኦ አስመልክቶ የሕይወት ልምዳቸውንና የስኬታማነት ምስጥሮቻቸውን አጋርተዋል፡፡

የፕሮግራሙ ተሳታፊ ተማሪዎች በአስተያየታቸው እንደገለጹት መሰል ፕሮግራሞች መዘጋጀታቸው ለተማሪው አስፈላጊና የማንቂያ ደወል በመሆናቸው በየጊዜው መሰል ፕሮግራሞች ቢዘጋጁ ከቀለም ትምህርት በተለየ የሕይወት ክሂሎት ግንዛቤ በማግኘት ስኬታማ ለመሆን የሚረዱ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት