Print

ለአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የግዢና ንብረት አስተዳደር እና የፋይናንስና በጀት አስተዳደር ባለሙያዎች እንዲሁም ለማኔጂንግ ዳይሬክተሮች በግዢ ዕቅድ፣ በግዢ መርሆዎች፣ በግዢ አፈፃፀም አቤቱታ አቀራረብ፣ በጨረታ ሰነድ ዝግጅትና የውል አስተዳደር እና በንብረት አስተዳደር ዕርሰ ጉዳዮች ላይ ከመጋቢት 08-09/2014 ዓ/ም ሥልጠና ተሰጥቷል፡፡ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

በመንግሥት ግዢና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ የግዢ ጥናትና መረጃ ትንተና ቡድን መሪ አቶ መልአኩ ተጓዴ እንደተናገሩት አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ነባርና ከፍተኛ በጀት የሚያንቀሳቅስ እንደመሆኑ የኦዲት ክፍተቶችን እንደግብአት በመውሰድ ስህተቶች እንዳይደገሙ የተሻለ የሥራ ሂደትን መከተል ይገባዋል፡፡ ስለሆነም ሥልጠናው የግዢ ዕቅድ፣ የግዢ መርሆዎችና የግዢ ዘዴዎችን በማሳየት አሠራሮችን ለማሻሻል የሚያስችል ነው ብለዋል፡፡

በኤጀንሲው የኦዲት ቁጥጥር ዳይሬክቶሬት ከፍተኛ ኦዲተር የሆኑት አቶ መማር መንግሥት ከዚህ ቀደም ኦዲት ሲያደርጉ በዩኒቨርሲቲው የጨረታ ሰነድ አለመጠቀም፣ ተጫራቾችን መገደብ፣ የግምገማ መስፈርት አለማስቀመጥ፣ ግዢን እየከፋፈሉ ከአንድ ድርጅት መግዛት የመሳሰሉ ስህተቶች መገኘታቸውን ገልጸው ሥልጠናው መሰል ስህተቶች እንዳይደገሙ የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የግዢና ንብረት አስተዳደር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ተወካይ አቶ ዘላለም ጌታቸው እንደገለጹት ለባለሙያዎቹና ለባለድርሻ አካላት በፌዴራል መንግሥት ከፍተኛ የግዢ ባለሙያዎች ሥልጠናው መሰጠቱ የተሻለ የግዢና የንብረት አስተዳደር ሥርዓት እንዲፈጠር ያግዛል፡፡ ሥልጠናው የነበሩባቸውን ክፍተቶች ለማሻሻል ብሎም ለ2015 የበጀት ዓመት ለሚያደርጉት ዝግጅት መነሻ እንደሚሆንም ተናግረዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ የግዢ ባለሙያና ሠልጣኞች አቶ ኤፍሬም መኮንን እና ወ/ሮ ትሁን ለማ በሰጡት አስተያየት የግዢ ክፍል ለብዙ ችግር ተጋላጭ በመሆኑ ሥልጠናው ዕውቀትን መሠረት ያደረገ ሥራ እንድንሠራ ያደርገናል ብለዋል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት