Print

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ኮሚዩኒቲ ት/ቤቶች የ2014 የትምህርት ዘመን 1ኛ ሴሚስተር አፈፃፀም ውይይትና የወላጅ በዓል የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራሮችና የተማሪ ወላጆች በተገኙበት መጋቢት 10/2014 ዓ/ም ተካሂዷል፡፡ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የኮሚዩኒቲ ት/ቤቶች ሥራ አስኪያጅ አቶ ሥላስ ጎዳና ፕሮ ግራሙ የተዘጋጀው በሴሚስተሩ የተማሪዎች ውጤትና ሥነ-ምግባር ከታለመው ዒላማ አንጻር ግብ መምታቱን ለመለካት እንዲሁም በተማሪዎች የትምህርትና የባህርይ ውጤት የወላጅና የመምህራን ድጋፍና ክትትል ያለውን ፋይዳ ለመገምገም መሆኑን ገልጸዋል፡፡
እንደ ሥራ አስኪያጁ ገለጻ ለመምህራን የሥራ ተነሳሽነት ማነቃቅያ ሥልጠናና ከአቻ ት/ቤቶች ጋር ልምድ ልውውጥ፣ መምህራንን በተለያዩ አደረጃጀቶች ማዋቀር፣ ለህፃናት ተማሪዎች መማሪያ አካባቢያቸውን ምቹ ማድረግ እና የመማሪያ መጻሕፍት ግዢ ከተከናወኑ ሥራዎች መካከል ይጠቀሳሉ፡፡

የተማሪዎች ሰዓት ማርፈድ፣ የትምህርት ግብዓት አሟልቶ አለመምጣት፣ የትምህርት ውጤታቸውን ለወላጅ ለማሳየት ፈቃደኛ አለመሆንና ሌሎችም የሥነ ምግባር ግድፈቶች፣ የተማሪ ቁጥር ከመማሪያ ክፍሎች ጋር አለመጣጣም፣ የግብዓት አለመሟላት፣ የሰው ኃይል ቅጥር መዘግየትና የመሳሰሉት ያጋጠሙ ችግሮች መሆናቸውን አቶ ሥላስ ተናግረዋል፡፡ ወላጆች በበኩላቸው የመማሪያ መጻሕፍት እጥረት፣ የትምህርት ክፍያ ምቹ አለመሆንና የሰርቪስ አሰጣጥ አጥጋቢ አለመሆን ችግሮችን አንስተዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው የምርምርና ማኅበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዝደንት ተ/ፕ በኃይሉ መርደኪዮስ የተማሪዎች ውጤት መዋዠቅ ችግሮችን ለመቅረፍ የተደረጉት ጥረቶች ለውጥ ማሳየታቸውን ተናግረው በተለይ ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚገቡ ተማሪዎች ቁጥር ካለፈው ዓመት መሻሻል የታየበት መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ከመማር ማስተማር ባሻገር በባህርይና በሥነ ልቦና ለማነጽ መምህር መሠረት በመሆኑ የመምህራንና የተማሪዎች ግንኙነት ጠንካራ ሊሆን እንደሚገባው ም/ፕሬዝደንቱ ተናግረዋል፡፡

በዩኒቨርሲቲው የሳይኮሎጂ ት/ክፍል መምህር የሆኑት አቶ አሊ ሙሳ የወላጆችን ኃላፊነትና እስከ ምን ድረስ ልጆቻቸውን ማገዝና መርዳት እንደሚችሉ ለወላጆች ሙያዊ ትንተና ሰጥተዋል፡፡ የልጆችን ጤንነትና ደኅንነት ማረጋገጥ፣ የማኅበረሰቡን ባህልና ወግ የሚያውቁ፤ የሚጠብቁና የሚንከባከቡ እንዲሆኑ ማስቻል እና ስኬታማ ለሆነ የአዋቂነት ዕድሜ እንዲዘጋጁ ማድረግ ትልቁ የወላጆች ድርሻ መሆኑን አቶ አሊ ጠቁመዋል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት