Print

አቶ ካሣሁን ደለለኝ ከአባታቸው ከአቶ ደለለኝ ታችበሌ እና ከእናታቸው ከወ/ሮ ዓለምነሽ ተረፈ በቀድሞ ጋሞ ጎፋ ክ/ሀገር በሳውላ ከተማ ነሐሴ 30/1976 ዓ.ም ተወለዱ፡፡

አቶ ካሣሁን ደለለኝ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን በሳውላ ከተማ በሚገኘው በቦትሬ መጀመሪያ ደ/ት/ቤት እንዲሁም የ2ኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በሳውላ 2ኛ ደረጃና መሠናዶ ት/ቤት ተከታትለዋል፡፡ አቶ ካሣሁን ከአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በኅብረተሰብ ጤና ፕሮግራም ዲፕሎማ ያገኙ ሲሆን በቀጣይም በአካባቢ ጤና (Environmental Health) ፕሮግራም በጅማ ዩኒቨርሲቲ የመጀመሪያ ዲግሪ ትምህርታቸውን ተከታትለው በማጠናቀቅ ተመርቀዋል፡፡ አቶ ካሣሁን በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በኅብረተሰብ ጤና (Public Health) ፕሮግራም በሳምንት መጨረሻ መርሃ-ግብር ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ የ2ኛ ዲግሪያቸውንም ትምህርት እየተከታተሉ ባሉበት ባደረባቸው ሕመም በሕክምና ሲረዱ ቆይተው መጋቢት 07/2014 ዓ/ም ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል፡፡

አቶ ካሣሁን ደለለኝ ከ1999 - 2007 ዓ.ም በኦይዳ ወረዳ፣ ከ2007 - 2008 ዓ.ም በደንባ ጎፋ ወረዳ፣ ከ2009 - 2010 ዓ/ም በጋሞ ጎፋ ዞን እንዲሁም ከ2010 ዓ/ም ጀምሮ ሕይወታቸው እስካለፈበት ቀን ድረስ በጎፋ ዞን ጤና ቢሮዎች ሕዝባቸውንና ሀገራቸውን አገልግለዋል፡፡

አቶ ካሣሁን ደለለኝ ባለትዳርና የአንዲት ሴት ልጅ አባት ነበሩ፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በአቶ ካሣሁን ደለለኝ ሞት የተሰማውን ሐዘን እየገለጸ ለቤተሰቦቻቸው፣ ለወዳጅ ዘመዶቻቸውና ለዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ መጽናትን ይመኛል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት