Print

የአርባ ምንጭ ውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ማኅበረሰብ አገልግሎት ማስተባበሪያ ጽ/ቤት በአርባ ምንጭ ዙሪያ ወረዳ ቆላ ሻራ ቀበሌ እያስጠገነ ያለውን የባዮ-ጋዝ ማብለያ ቴክኖሎጂ የመጀመሪያ ዙር ሳይት ምልከታ መጋቢት 14/2014 ዓ/ም አካሂዷል፡፡ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ተክሉ ወጋየሁ እንደገለጹት የባዮ-ጋዝ ቴክኖሎጂ እርጥብ ቆሻሻ፣ የእንስሳት ዕዳሪ፣ የሰው ዓይነ-ምድርና የእርሻ ተረፈ ምርትን በመጠቀም ኃይል የሚያመነጭ ቴክኖሎጂ ነው፡፡ በአሁኑ ሰዓት እንደ ሀገር በቴክኖሎጂው ላይ ያለው ዕይታ መቀየሩንና በመንግሥት በኩልም ትልቅ ትኩረት የተሰጠው የቴክኖሎጂ ዘርፍ መሆኑን ዶ/ር ተክሉ ተናግረዋል፡፡

እንደ ዶ/ር ተክሉ ገለጻ ምልከታ የተደረገባቸው የባዮ ጋዝ ማብለያዎች ከዚህ ቀደም በ“SNV” ፕሮጀክት የተሠሩ ሲሆን በገጠሟቸው ብልሽቶች አገልግሎት መስጠት አቁመው ነበር፡፡ በመሆኑም የማኅበረሰብ አገልግሎት በየዓመቱ ለመምህራን በምርምር ፕሮጀክት ዘርፍ በሚያወጣው ማስታወቂያ መሠረት ‹‹የባዮ-ጋዝ ቴክኖሎጂ ጥገና በቆላ ሻራና በጫኖ ሚሌ ቀበሌያት›› በሚል ርዕስ በቀረበው ፕሮፖዛል በቆላ ሻራ ቀበሌ በመጀመሪያ ዙር 30 አባወራዎችን ተጠቃሚ ለማድረግ የጥገና ሥራው ታቅዷል፡፡ በዚህም መሠረት 25ቱ ሙሉ በሙሉ ተጠግነው ወደ ሥራ የገቡ ሲሆን 5ቱ በሂደት ላይ ናቸው ብለዋል፡፡  

በቀበሌው ከSNV ፕሮጀክት በተጨማሪ ዩኒቨርሲቲው ከደቡብ ክልል ማዕድንና ኢነርጂ ቢሮ እና ከዞኑ ውሃ፣ ማዕድንና ኢነርጂ መምሪያ ጋር በመተባበር ያሠራቸው ዘመናዊ የባዮ-ጋዝ ማብለያ ቴክኖሎጂዎች መኖራቸውን ዶ/ር ተክሉ ጠቅሰዋል፡፡ ቴክኖሎጂዎቹ በአነስተኛ ብልሽት አገልግሎት እንዳያቆሙ ኅብረተሰቡ እንደ ማንኛውም ኤሌክትሮኒክስ መሣሪያ አስጠግኖ እንዲጠቀም በአካባቢው ሥራ-አጥ ወጣቶችን አደራጅቶ ሥልጠና በመስጠት ወደ ሥራ ለማስገባት ቀጣይ አቅጣጫ መያዙንም ተናግረዋል፡፡  

የውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ማኅበረሰብ አገልግሎት አስተባባሪ መ/ርት ፌቨን ክንፈ በበኩላቸው በምርምር የተገኙ ውጤቶችን ወደ ማኅበረሰቡ ማሸጋገርና የማኅበረሰቡን ችግር መቅረፍ አንዱ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተልኮ መሆኑን ጠቅሰው በጥገና ፕሮጀክቱ 2 መቶ ሺህ ብር ወጪ በማድረግ በመጀመሪያ ዙር 30 አባወራዎችን ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡

የውሃ አቅርቦትና የአካባቢ ምኅንድስና ፋከልቲ ዲን፣ ተመራማሪና የፕሮጀክቱ ዋና አስተባባሪ መ/ር ዘነበ አመለ በአርባ ምንጭ ዙሪያ ወረዳ ከተሠሩ የባዮ-ጋዝ ማብለያ ፕሮጀክቶች ውስጥ ከግማሽ በላይ የሚሆኑት አገልግሎት መስጠት ማቆማቸውን በመገንዘብ ያቀረቡት ጥናታዊ ጽሑፍ ተቀባይነት በማግኘቱ ከ2012 ዓ/ም ጀምሮ ወደ ሥራ ቢገቡም በግዢ ሂደት መጓተት ምክንያት እስከ አሁን መዘግየታቸውን ተናግረዋል፡፡

አክለውም አጠቃላይ ለፕሮጀክቱ ከተመደበው በጀት በ1 መቶ ሺህ ብር የባዮ-ጋዝ መስመር መቆጣጠሪያ፣ መዝጊያና መክፈቻ (ጌት ቫልቭ)፣ የጋዝ መለኪያ፣ አምፖልና የአምፖል ክር፣ ለመስመር ዝርጋታ የሚያገለግሉ ባለ 10 ሚ.ሜ ሆዝ

በአጠቃላይ 30 ሜትር ለ30 አባወራ ቤት አገልግሎት የሚሰጥና ለሌሎችም መሠረታዊ የባዮ-ጋዝ ዕቃዎች ግዢ ውሏል ብለዋል፡፡

የቆላ ሻራ ቀበሌ ነዋሪና የባዮ-ጋዝ ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ የሆኑት ወ/ሮ ፈለቀች ዶላ ከዚህ ቀደም ባዮ-ጋዝን ሲጠቀሙ መቆየታቸውንና በቤት እድሳት ወቅት አንዳንድ ዕቃዎች በመበላሸታቸው ለ2 ዓመታት መጠቀም አቁመው መቸገራቸውን ተናግረዋል፡፡ አሁን ላይ የተጓደሉ ቁሳቁሶች ተሟልተው አገልግሎት እያገኙ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

የባዮ-ጋዝ ቴክኖሎጂ ግንባታ ባለሙያና የቀበሌው ነዋሪ አቶ ማቲዮስ ማርጮ የባዮ-ጋዥ ቴክኖሎጂ መሣሪያዎች ብልሽት ሲያጋጥማቸው የተብላሉ ፈሳሾች ቶሎ የሚደርቁና ዝገት የሚያጋጥም መሆኑን ገልጸው ብልሽት ሲያጋጥም መሣሪዎች በቶሎ ቢቀየሩ ለማኅበረሰቡ ጥሩ አገልግሎት መስጠት ያስችላል ብለዋል፡፡

በፕሮግራሙ የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ማኅበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ተክሉ ወጋየሁ፣ የውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ማኅበረሰብ አገልግሎት አስተባባሪ፣ የፕሮጀክቱ አስተባባሪዎችና ባለሙያዎች ተገኝተዋል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት