በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የሕግ ትምህርት ቤት አዘጋጅነት ‹‹Public Diplomacy for Global Cooperation›› በሚል ርዕስ በኢትዮጵያ፣ ጅቡቲና አፍሪካ ኅብረት የኢንዶኔዢያ አምባሳደር አል ቡስራ ባስኑር (Al Busyra Basnur) መጋቢት 15/2014 ዓ/ም በዩኒቨርሲቲው ተገኝተው ገለጻ አድርገዋል፡፡ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

አምባሳደር አል ቡስራ ባደረጉት ገለጻ ፐብሊክ ዲፕሎማሲ መንግሥት በመዋቅር በሚሠራው ሀገራዊ የገጽታ ግንባታ ላይ እያንዳንዱ ዜጋ ስለ ሀገሩ የሚቆምበትና መልካም ገጽታ እንዲገነባ በሚያገኘው አጋጣሚ ሁሉ የበኩሉን ድርሻ የሚወጣበት ነው ብለዋል፡፡

አምባሳደሩ አክለውም ሀገራቸው ኢንዶኔዥያ ‹‹ኢንዶኔዢያ ዩዝ ኮንግረስ (Indonesia Youth Congress)››ን በሀገር ደረጃ በማቋቋምና መዋቅሩን ተጠቅሞ በወጣቶች በተለይም ፐብሊክ ዲፕሎማሲን በተደራጀ ሁኔታ በመተግበር የኢንዶኔዥያን በጎ ገጽታ ለዓለም ለማስተዋወቅ ብሎም ኢንዶኔዥያ እንደ ሀገር እንዲከበሩላት የምትፈልጋቸው መብቶች በዓለም አቀፍ ደረጃ እንዲከበሩላት እድል የሰጣት መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ይህም ኢትዮጵያ አሁን ባለችበት ፖለቲካዊ ሁኔታና ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በተለይም ምዕራባውያን የሚፈጥሩትን ወቅታዊ ጫና ለመቋቋም ፐብሊክ ዲፕሎማሲ ወሳኝ ሚና የሚጫወት በመሆኑ ወጣቶችን ጨምሮ ሁሉም ዜጋ ባለው አቅምና ዕውቀት ስለሀገሩ መልካም ገጽታ መፍጠር እንደሚችል የሚያሳይ ነው ብለዋል፡፡

አምባሳደሩ ኢንዶኔዥያ ነፃነቷን ለማረጋገጥ የመጣችበት መንገድ አጭር ታሪካዊ ዳሰሳ፣ የወጣቶችን አቅም በመጠቀም ረገድ ያላትን ተሞክሮ፣ ኢትዮጵያና ኢንዶኔዥያ ያላቸው የዲፕሎማሲ ግንኙነትና በቀጣይም በሁለቱ ሀገራት ትብብር ሊሠሩ በሚችሉ የትምህርት፣ የምርምርና የኢኮኖሚ አማራጮች ዙሪያ ማብራሪያ አቅርበዋል፡፡ አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ኢንዶኔዥያ ከሚገኙ 17 ዩኒቨርሲቲዎች ጋር የጋራ ስምምነት የተፈራረመ መሆኑን የተናገሩት አምባሳደሩ ሀገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር በተለያዩ ዘርፎች በትብብር ለመሥራት ፍላጎት ያላት መሆኑን ገልጸዋል፡፡ 

የዩኒቨርሲቲው የምርምርና ማኅበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዝደንትና የፕሬዝደንት ተወካይ ተ/ፕ በኃይሉ መርደኪዮስ እንደገለጹት የዲፕሎማሲ ሥራ በሀገራት ፖለቲካዊ፣ ምጣኔ ሀብታዊ፣ ፖሊሲ እና በዜጎች የጋራ ተጠቃሚነት ጉዳዮች ላይ የሚያተኩርና የበለጸጉ ሀገራት በሌሎች ሀገራት ላይ ተጽዕኖ ለማሳረፍ ስልታዊ ወዳጅነትን ለማጠናከር የሚጠቀሙበት መሣሪያ ነው፡፡ የዲፕሎማሲ ሥራ አካል የሆነው ፐብሊክ ዲፕሎማሲ በሀገራት መካከል የጋራ ጥቅም ትብብርና መተማመን እንዲፈጠር ጉልህ አስተዋጽኦ አለው ብለዋል፡፡

ተ/ፕ በኃይሉ በአሁኑ ወቅት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ማኅበረሰብ ሀገራቸውን በተገቢው ሁኔታ እንዲያገለግሉና ስለ ሀገራቸው ወቅታዊ ሁኔታ በቂ ግንዛቤ እንዲኖራቸው ለማስቻል የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር በመተባበር በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ማዕከላት እንዲቋቋሙ ማድረጉን ም/ፕሬዝደንቱ ጠቁመዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው የሕግ ት/ቤት ዲን መ/ር እንየው ደረሰ በበኩላቸው ፕሮግራሙ ፐብሊክ ዲፕሎማሲ ለሀገራችን ያለውን ፋይዳ ለማስገንዘብ፣ ኢትዮጵያ እየደረሰባት ካለው የምዕራባውያን ሀገራት ጫና ለመከላከል የምትችልበት የፐብሊክ ዲፕሎማሲ አማራጮችን ለማሳየትና ሀገራችን በቀጣይ ምን ማድረግ እንዳለባት የተሻሉ ተሞክሮዎችን ለመውሰድ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በፕሮግራሙ የተለያዩ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ተነስተው አምባሳደር አል ቡስራ ከሕይወት ልምዳቸው አንጻር ምላሽ ሰጥተውባቸዋል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት