Print

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ሥነ-ትምህርትና ሥነ-ባህሪ ሳይንስ ት/ቤት ‹‹Enhancing Community Development in Malo Koza Woreda›› በሚል ርዕስ በመሎ ኮዛ ወረዳ ላሃ ከተማ መጋቢት 17/2014 ዓ.ም የምርምር ውጤት ማረጋገጫ ወርክ ሾፕ አካሂዷል፡፡ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የምርምር ፕሮጀክቱ መሎ ኮዛ ወረዳና አካባቢው ያለውን እምቅ የተፈጥሮ ሀብት በአግባቡ የመጠቀም አቅምን ለማሳደግ ያለመ ሲሆን ትምህርት፣ ግብርና፣ ጤና፣ መንገድ፣ ወንጀል መከላከልና የመሳሰሉ ዘርፎችን ያካተተ መሆኑን የጥናታዊ ጽሑፉ አቅራቢ ዶ/ር ቤታ ፃማቶ ገልጸዋል፡፡ ዶ/ር ቤታ ወረዳውና አካባቢው የኮረሪማ፣ ዝንጅብል፣ ቡና፣ ማንጎ፣ አቮካዶ፣ ሙዝ፣ ጤፍ፣ በቆሎ እንዲሁም የእንሰት ምርት ያለበት መሆኑን ተናግረው ከምርቶቹ ለውጪ ገበያ የሚሆኑትን በመለየትና የተሻለ የገበያ ትስስር በመፍጠር የውጭ ምንዛሪ ለማግኘት ሣይንሳዊ በሆነ መንገድ ቢሠራ የማኅበረሰቡን የኑሮ ደረጃ ማሻሻል የሚያስችል እምቅ አቅም አለው ብለዋል፡፡

የምርምርና ማኅበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዝደንት ተ/ፕ በኃይሉ መርደኪዮስ እንደተናገሩት ዩኒቨርሲቲው የመጀመሪያ ትውልድ ዩኒቨርሲቲ ከሚባሉት መካከል እንደመሆኑ የማኅበረሰቡን ችግር የሚፈቱና ለሀገር የሚጠቅሙ ምርምሮችን ይሠራል፡፡ የመሎ ኮዛ አካባቢ ማኅበረሰብ ምርቱን ለገበያ ለማቅረብ በተለያዩ ምክንያቶች ለረዥም ጊዜ ዕድል ያላገኘ መሆኑን ጥናታዊ ጽሑፉ ያሳያል ያሉት ም/ፕሬዝደንቱ አሁን ላይ የተጀመረው ፕሮጀክት በመሠረተ ልማት፣ በግብርና፣ በፍራፍሬ፣ በሰብል ምርትና በወንጀል መከላከል ጉዳዮች የማኅበረሰቡን ተጠቃሚነትና ተደራሽት ለማረጋገጥ የሚሠራና ሰፊ ይዘት ያለው መሆኑን ገልጸዋል፡፡

እንደ ተ/ፕ በኃይሉ ማኅበረሰብና መንግሥት በመተባበር የሚሠሩት ሥራ ለሀገር የሚያበረክተው አስተዋፅኦ ከፍተኛ እንደመሆኑ ትምህርት፣ ጤና፣ ንጹህ የመጠጥ ውሃ፣ መንገድና የመሳሰሉት ሊያስተሳስሩ የሚችሉ መሠረተ ልማቶች አስፈላጊ ናቸው፡፡የምርምር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ተስፋዬ ሀ/ማርያም በበኩላቸው ፕሮጀክቱ ምርምርንና የማኅበረሰብ አገልግሎትን በአንድ ላይ አቀናጅቶ የያዘ፣ የ3 ዓመት ቆይታ ያለውና አንድ ሚልየን ብር የተመደበለት መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ፕሮጀክቱ ማኅበረሰቡንና የወረዳ ሴክተር መሥሪያ ቤቶችን የሚያሳትፍ ነው ያሉት ዳይሬክተሩ የአካባቢው ማኅበረሰብ የእርሻ ማሳውን ለመንገድ ሥራ በፈቃዱ እስከ መስጠት ያለውን ተነሳሽነትና የልማት ተሳትፎ አድንቀዋል፡፡የመሎ ኮዛ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ኤርምያስ ወሰኔ እንደገለጹት በአካባቢያቸው በምርምር፣ በመስኖ ሥራ፣ በትምህርትና በሌሎችም የተለያዩ ዘርፎች አርሶ አደሩን ለመደገፍ በመምጣት ዩኒቨርሲቲው የመጀመሪያው ተቋም ነው፡፡ ወረዳው ለፕሮጀክቱ ቅድሚያ ሰጥቶ እየሠራ ነው ያሉት አቶ ኤርሚያስ የጀመርነውን የልማት ጉዞ በሌሎችም ዘርፎች አጠናክረን እንሠራለን ብለዋል፡፡

በመንገድ ሥራው ላይ የዲዛይንና የማማከር ሥራ የሚሠሩት ኢንጂነር ባህሩ ባይከዳኝ ከመንገድ ፕሮጀክቱ አንዱ የሆነውና ቦክሬ፣ ቶባና ዳላ ቀበሌያትን የያዘው የ9 ኪ.ሜ መንገድ የመጀመሪያ ዙር የአፈር ቆረጣ ሥራ መጀመሩን፣ የመንገድ ትስስሩ በጣም ጠባብ በመሆኑ ኅብረተሰቡን ባማከለ መልኩ መቆፈሩንና ሦስቱን ቀበሌያት በቀላሉ እየሚያገናኝ ተናግረዋል፡፡አርሶ አደር አባተ አሻ በቀደሙት ዓመታት በእግራቸው ረዥም መንገድ በመጓዝ እንደሚገበያዩ ተናግረው አሁን ላይ የመንገድ ሥራው በመጀመሩ የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል፡፡

ለመንገድ ልማቱ መሬታቸውን መስጠታቸውን የገለጹት አርሶ አደሩ አካባቢው መልማቱ ነገ ልጆቻችንና የልጅ ልጆቻችን በዘመናዊ መንገድ ተንቀሳቅሰው ለመሥራት ምቹ ዕድል እንደሚፈጥርላቸው ተስፋ አለኝ ብለዋል፡፡ በቀጣይ ከግብርና ባለሙያዎች ጋር በመመካከር ሙዝ፣ አቮካዶ እና የመሳሰሉትን ለመትከል ዝግጁ መሆናቸውንም ተናግረዋል፡፡

በወርክ ሾፑ የዩኒቨርሲቲው አመራሮች፣ የጎፋ ዞን አስተዳደር ተወካይ፣ የወረዳው አስተዳደርና አመራሮች፣ የፀጥታ አካላት፣ የሃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች፣ የቀበሌ አስተዳደሮችና የአርሶ አደር ተወካዮች የተገኙ ሲሆን በፕሮግራሙ መጨረሻ በአርሶ አደሩና በወረዳው ሴክተር መሥሪያ ቤቶች ተሳትፎ የመጀመሪያ ዙር የአፈር ቆረጣ ሥራ የተጀመረለትን መንገድ ጎብኝተዋል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት