Print

የሴቶችን አቅም ከማጎልበት፣ ከሕግና ከሥልጠና ድጋፎች አንጻር አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በማኅበረሰብ አገልግሎት ዘርፍ ለሠራቸው ሥራዎች የጨንቻ ዙሪያ ወረዳ ሕዝብ ምክር ቤት መጋቢት 19/2014 ዓ/ም የዕውቅና ምስክር ወረቀት አበርክቷል፡፡ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የምስክር ወረቀቱን የምክር ቤቱ ዋና አፈ ጉባኤ፣ የሕግ ማውጣትና የተቋማት ክትትልና ቁጥጥር ቡድን መሪ እና የሴቶችና ሕፃናት ማኅበራዊ ዘርፍ ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አበርክተዋል፡፡
የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በማኅበረሰብ አገልግሎት ዘርፍ ሰፊ ሥራዎችን እያከናወነ እንደሆነ ገልጸው ዕውቅናው በምክር ቤት አፈ ጉባኤ ደረጃ መሰጠቱ ያስደሰታቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የማኅበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ተክሉ ወጋየሁ እንደገለጹት የማኅበረሰብ አገልግሎት ሥራዎች ፍላጎት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገና እየጨመረ ሲሆን አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲም በጋሞ ዞን፣ በጎፋ ዞን፣ ኮንሶ ዞን፣ ጂንካ፣ ቡርጂ፣ አማሮና በዩኒቨርሲቲው አቅራቢያ ባሉ ከተሞችና ወረዳዎች ሰፊ ተደራሽነት አለው፡፡

እንደ ዶ/ር ተክሉ ገለጻ ጨንቻ ዙሪያ ወረዳ ዘንድሮ የተጀመረ የተቀናጀ ተግባር ተኮር የጎልማሶች ትምህርት፣ በዋናነት ሴቶች፣ ሕፃናትና አቅመ ደካሞችን በፍትህ የሚደግፉ ነፃ የሕግ አገልግሎት መስጫ ማዕከላት፣ የመኖ ሣር የሚያመርቱ ችግኝ ጣቢያዎች እና የሳሃይ ሶላር ፕሮጀክት ተጠቃሚ ወረዳ ነው፡፡

በወረዳው ምርምርን መነሻ በማድረግ ዶርዜ ላይ ቀርከሃን በዘመናዊ መልክ ለቤት ውስጥ ቁሳቁስ በማዋል ገቢ መፍጠር፣ የድንችና አፕል ዘር የማሰራጨት እንዲሁም በዶርዜ የእንሰት ምርምር ማዕከል ተበትነው ያሉ የተለያዩ የእንሰት ዝርያዎችን የመሰብሰብ ሥራዎች የተሠሩ ሲሆን የግርጫ ማዕከልን ተከትሎ ሁለት ቀበሌያት የሃይድሮ ኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ እንዲሆኑ ተደርጓል፡፡

የጠዬ ወንዝ ድልድይ የመሥራት ዕቅድ መያዙንና የመጠጥ ውሃን በተመለከተ ክንውኖች ጅምር ላይ መሆናቸውን ዶ/ር ተክሉ ተናግረዋል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት