የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ሴቶች፣ ሕፃናትና ወጣቶች ዳይሬክቶሬት በዓለም ለ111ኛ በሀገራችን ለ46ኛ ጊዜ የተከበረውን ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን ‹‹እኔ የእህቴ ጠባቂ ነኝ›› በሚል መሪ ቃል መጋቢት 15/2014 ዓ/ም የካምፓሱ ማኔጂንግ ዳይሬክተር፣ ሴት የአስተዳደር ሠራተኞችና ሴት ተማሪዎች በተገኙበት በሳውላ ካምፓስ አክብሯል፡፡ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የዳይሬክቶሬቱ የሴቶችና ሕፃናት ጉዳዮች ቡድን መሪ አቶ ዛፉ ዘውዴ ባቀረቡት ሰነድ እንዳብራሩት በዓሉ የሚከበርበት ዋነኛ ዓላማ በዓለም ያሉ መንግሥታት የሴቶች ጉዳይ የልማት፣ የመልካም አስተዳደርና የዲሞክራሲ ጉዳይ እንደሆነ አምነው በመቀበል በሴቶች ዙሪያ ፖሊሲዎቻቸውን፣ ሕጎቻቸውንና አሠራሮቻቸውን በመፈተሽ በሴቶች ላይ የሚፈፀሙ መድልኦዎችን እንዲያስወግዱና የሴቶችን ተሳታፊነትና ተጠቃሚነት እንዲያረጋግጡ ለማነሳሳት ነው፡፡

በተጨማሪም በዓሉ ሴቶች በድንበር፣ በሃይማኖት፣ በቀለም፣ በቋንቋና በባህል ሳይለያዩ የሚደርስባቸውን ጭቆናና መድልኦ የሚያወግዙበት፣ አንድነታቸውን የሚያጠናክሩበት፣ ድምጻቸውን በጋራ የሚያሰሙበት፣ ለነፃነት፣ ለፍትሕና ለእኩልነት ያደረጉትን ተጋድሎ የሚዘክሩበት፣ ልምድ የሚለዋወጡበትና ለበለጠ ትግል ተቀናጅተው ለመንቀሳቀስ ቃል የሚገቡበት ነው ብለዋል፡፡

የካምፓሱ ማኔጂንግ ዳይሬክተር ወ/ሮ ገነት ጥላሁን ሴቶች በተሰማሩበት በየትኛውም የሙያ ዘርፍ ሁሉ አቅማችንንና ጊዜያችንን በአግባቡ ከተጠቀምን ለስኬት የማንበቃበት ምክንያት እንደማይኖር ገልጸው ሴቶች የተለያዩ መልካም አጋጣሚዎችን በመጠቀም እችላለሁ በሚል መንፈስ ከሠራን ከተሻለ ስኬት እንደርሳለን ብለዋል፡፡

የሳውላ ካምፓስ የኤች አይ ቪ/ኤድስና የሥነ ተዋልዶ ጉዳይ ባለሙያ ወ/ሮ ትምኒት ግደይ በዓሉ ሴት ተማሪዎችንና ሠራተኞችን ያነቃቃ መሆኑንና መሰል ፕሮግራሞች በዓል ተጠብቆ ሳይሆን በየጊዜው በሥልጠናዎችና በግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኮች ቢካተቱ ሴቶችን ይበልጥ የሚያበረታቱ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በየዓመቱ የላቀ ውጤት እያስመዘገበች የምትገኘው የ5ኛ ዓመት የምግብ ምኅንድስና ተማሪ እድላዊት በረከት ለሴት ተማሪዎች ልምዷን ስታካፍል ጊዜዋን በአግባቡ መጠቀሟ፣ ትምህርቷ ላይ ትኩረት ማድረጓና የራሷን የአጠናን ዘዴ መከተሏ ለውጤት ያበቃት መሆኑን ተናግራለች፡፡ በተጨማሪም ለዕቅድ መገዛት፣ በራስ የመተማመን ስሜትንና የማንበብ ልምድን ማዳበርና ማንኛውንም ጓደኛ ከዓላማ አንፃር መርጦ መያዝ የስኬት ቁልፍ መሆኑን ገልጻለች፡፡

በፕሮግራሙ የተካሄደውን ውይይት ተከትሎ ጥያቄዎችና አስተያየቶች የቀረቡ ሲሆን ከሚመለከታቸው አካላት ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል፡፡ ከፍተኛ ውጤት ላመጡ ሴት ተማሪዎችም ሽልማት ተበርክቶላቸዋል፡፡