አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ‹‹The Economics of Land Degradation Initiative››፣ ‹‹GRÓ, Land Restoration Training Program›› ከተሰኙ መቀመጫቸውን ጀርመንና አይስላንድ ካደረጉ ተቋማትና GIZ ኢትዮጵያ ጋር በመተባበር ‹‹Integrated Approaches for Land Restoration through Sustainable Land and Aquatic Management›› በሚል ርዕስ ከጫሞ ተፋሰስ 10 ወረዳዎች ለተወጣጡ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ባለሙያዎችና የሥራ ኃላፊዎች ከመጋቢት 19-23/2014 ዓ/ም ለ5 ቀናት የቆየ ሥልጠና ተሰጥቷል፡፡ 

ሥልጠናው ከአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲና ከሦስቱ ተቋማት በተወጣጡ የዘርፉ ምሁራን በገጽ ለገጽና በኦንላይን የተሰጠ ሲሆን ሠልጣኞች በጫሞ ሐይቅ፣ በገረሴ ጌዣ ጥብቅ ደንና በደንብሌ ቀበሌ ተገኝተው በስፍራዎቹ እየተከናወኑ ያሉ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራዎችን እንዲሁም የደረሱ ጉዳቶችን የመስክ ምልከታ አድርገዋል፡፡  ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የዩኒቨርሲቲው የምርምርና ማኅበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዝደንት ተ/ፕ በኃይሉ መርደኪዮስ በመክፈቻ ንግግራቸው መሬት ከሰዎች ሕይወት ጋር የማይነጠል ትስስርና ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያለው ሀብት መሆኑን ጠቁመው በመሬት መራቆት ምክንያት በኢትዮጵያ ደጋማ አካባቢዎች የግብርና ምርት መቀነስ እየተስተዋለ ነው ብለዋል፡፡ በዚህም የምርት መቀነስና ሌሎች ተያያዥ ምክንያቶችን መሠረት በማድረግ መንግሥት በሀገሪቱ 6 ክልሎች የሚገኙ 209 ወረዳዎች ላይ ዘላቂ የመሬት አስተዳደር ፕሮግራም ቀርፆ ተግባራዊ እያደረገ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

በሐይቆች ዙሪያ የሚሠሩ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራዎች ሐይቆቹንና በውስጣቸው የሚገኘውን ብዝሃ ሕይወት ከመጠበቅ አንፃር ፋይዳቸው የጎላ በመሆኑ በዘርፉ የሚሠሩ የምርምር እና የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራዎች ትኩረት ሊሰጣቸውና ሳይንሳዊ አሠራርን የተከተሉ ሊሆኑ እንደሚገባም ም/ፕሬዝደንቱ አሳስበዋል፡፡ ዓባያና ጫሞ በታላቁ ስምጥ ሸለቆ ውስጥ ከሚገኙ ትልልቅ ሐይቆች መካከል መሆናቸውን የተናገሩት ም/ፕሬዝደንቱ በሐይቆቹ ዙሪያ የሚሠሩ ዘላቂ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራዎች ሐይቆቹን ከተጋረጠባቸው የጨዋማነት፣ የምግብ ሰንሰለት መዛባት፣ የዓሳ ምርት መቀነስ ወዘተ አደጋዎች ከመከላከል አንፃር የማይተካ ሚና የሚጫወት መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ከዚህም አንፃር አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ከሌሎች አጋር አካላት ጋር በመሆን በመስኩ የጀመረው የባለሙያዎችን አቅም በሳይንሳዊ ዕውቀት የመገንባትና በመስኩ የጀመራቸውን የምርምርና ተግባራዊ ሥራዎችን አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡

ከሥልጠናው አስተባባሪዎችና አሠልጣኞች መካከል አንዱ የሆኑት የAMU-IUC ፕሮግራም ኃላፊ ዶ/ር ፋሲል እሸቱ ዘላቂ የአፈርና ውሃ አያያዝ ዘዴ የተፈጥሮ ሀብትን ሰውም ተፈጥሮም ሳይጎዳ በዘላቂነት መጠቀም የሚያስችል ሳይንሳዊ መንገድ መሆኑን ጠቁመው ይህም ለጊዜያዊ ጥቅም ሲባል በተፈጥሮ ሀብቶቻችን ላይ የሚደርሰውን ጉዳት የሚያስቀር ነው ብለዋል፡፡ አፈር በፕላኔታችን ከሚገኙ እጅግ ወሳኝ ሀብቶች መካከል ዋነኛው መሆኑን የገለጹት ዶ/ር ፋሲል ለባለሙያዎቹ የተሰጠው የትብብር ሥልጠናም ዘላቂ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ ውሃን በማካተት የሐይቆችን ተፋሰስ መሠረት አድርጎ መሠራት አለበት የሚለውን መርህ በተከተለና ተግባራዊ ማድረግ በሚያስችል መልኩ የተሰጠ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ የአፈር አፈጣጠርና መራቆት ሂደት፣ የመሬት መራቆት በውሃ ሥነ-ምኅዳር ላይ የሚያመጣው ተጽዕኖ፣ የመሬት መራቆት ኢኮኖሚክስ- የመሬት መራቆት ኪሳራ ትንተና፣ የተራቆተ መሬትን ወደ ነበረበት መመለስና ለሥራው የሚያስፈልግ የገንዘብ

መጠንን ለመተመን የሚያስችሉ ዘዴዎች የሚሉትና ሌሎች ሥልጠናው የተሰጠበቸው የትኩረት ነጥቦች መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ መምህር፣ ‹‹The Economics of Land Degradation Initiative›› አስተባባሪና አሠልጣኝ ዶ/ር መስፍን ጥላሁን በበኩላቸው ሥልጠናው በመሬት መራቆትና በዘላቂ የመሬት አያያዝ ዙሪያ በዓለም አቀፍና በሀገር ደረጃ ያሉ እውነታዎችን ለሠልጣኞች ማሳወቅን፣ ሠልጣኞች ተግባር ላይ ያተኮረ ዘላቂ የመሬት አያያዝ ሥራ ፕሮጀክት መንደፍ እንዲችሉ ማድረግና በመሬት መራቆትና መሬትን ወደ ነበረበት የመመለስ ኢኮኖሚክስ ዙሪያ ግንዛቤ መፍጠርን ዓለማ በማድረግ የተዘጋጀ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በተጨማሪም በመሬት መራቆት ሳቢያ የደረሰ ኪሳራን ወደ ገንዘብ መቀየር፣ መሬቱን ወደ ነበረበት ለመመለስ የሚያስፈልግ ወጪን መተመንና ዘላቂ የመሬት አያያዝ ለማከናወን የሚያስፈልግ የአዋጭነት ጥናት ለማከናወን የሚረዱ ዘዴዎችን ለሠልጣኞች ማሳወቅና በተግባር መሞከር ሌላኛው የሥልጠናው ትኩረት መሆኑንም ዶ/ር መስፍን ጠቁመዋል፡፡

ከሠልጣኞች መካከል ከአርባ ምንጭ ዙሪያ ወረዳ የመጡት የተፋሰስ ልማት ባለሙያው አቶ ሲሳይ ቢያ በሥልጠናው ከሥራቸው ጋር ተዘማጅ የሆኑ በርካታ አዳዲስ ዕውቀቶችን እንደገበዩ ተናግረው ዘላቂ የአፍርና ውሃ ጥበቃ ሥራዎችን በተመለከተ የሚከናወኑ አካላዊና ሥነ-ሕይወታዊ ሥራዎች ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ ለማከናውን የሚያስችሉ መንገዶችን ማወቃቸውን ገልፀዋል፡፡ በሥልጠናው የመስክ ምልከታ ክፍለ ጊዜም የተፈጥሮ ሀብቶችን ለመጠበቅ፣ የተጎዱ የተፈጥሮ ሀብቶች ተመልሰው እንዲያገግሙ የሚያስችሉ ሳይንሳዊ መንገዶችን እንዲሁም የተፈጥሮ ሀብቶችን በአግባቡ አለመጠቀም የሚያስከትለውን ዘርፈ ብዙ ጉዳት በተግባር ያዩበትና ለቀጣይ ሥራቸው ተሞክሮ የቀሰሙበት እንደሆነም ተናግረዋል፡፡

ከደራሼ ልዩ ወረዳ የመጡት የተፍጥሮ ሀብት ባለሙያው አቶ ኩስያ ጉዳይቶ በበኩላቸው ደራሼና አካባቢው የሚኖረው ማኅበረሰብ በባህላዊ መንገድ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ የማከናወን የዳበረ ልማድ እንዳለው ተናግረው በሥልጠናው ይህንን የማኅበረሰቡን ባህላዊ የአፈርና ጥበቃ ሥራ ሳይንሳዊ አሠራሮችን በመከተል ማዘመን የሚያስችሉ ግንዛቤዎችን ማግኘታቸውን ገልፀዋል፡፡ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ ሲሰራ ትርፍና ኪሳራ ታሳቢ አይደረግም ያሉት አቶ ኩስያ በሥልጠናው ዘላቂ የአፍርና ውሃ ጥበቃ ሥራ ለማከናውን የአዋጭነት ጥናት ማከናውን እንደሚገባና የመስኩን አሠራሮችንም እንዳወቁ ጠቁመዋል፡፡

የአካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር ዓለማየሁ ጩፋሞ በመዝጊያ ንግግራቸው የተፈጥሮ ሀብቶቻችንን ብሎም ሐይቆችን ከተጋረጠባቸው አደጋ ለመታደግ የሚከናወኑ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራዎች ወሳኝ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡ በመስኩ የሚሠሩ ባለሙያዎችን በዕውቀትና ክሂሎት ለማጎልበት ከዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር በመተባበር የተሰጠው ሥልጠና ጠቀሜታው ዘርፈ ብዙ ነው ያሉት ዶ/ር ዓለማየሁ ሠልጣኞች ከሥልጠናው ያገኙትን ዕውቀት ወደ ተግባር መለወጥ እንደሚጠበቅባቸውም አሳስበዋል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት