Print

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ሴቶች፣ ሕፃናትና ወጣቶች ዳይሬክቶሬት ሴቶች በሚደርስባቸው ጾታዊ ትንኮሳ፣ አድልኦ፣ የሥራ ጫና፣ ከወንዶች እኩል አለመታየትና በሌሎችም ርዕሰ ጉዳዮች ዙሪያ መጋቢት 21/2014 ዓ/ም ውይይት አካሂዷል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ሴቶች፣ ሕፃናትና ወጣቶች ጉዳይ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወ/ሪት ሠናይት ሳህሌ የአመለካከት ችግሮች ሴቶችን ወደ ኋላ ያስቀሩ መሆኑን ገልጸው ያለ ሴቶች ተሳትፎ ስኬታማ መሆን እንደማይቻል በመረዳት በዓለም አቀፍ ደረጃ ሀገራት የሴቶችን ጉዳይ አካተው መሥራት ጀምረዋል ብለዋል፡፡  ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

ሴቶች በአመራርና በውሳኔ ሰጪነት እንዲሳተፉ በመንግሥት ደረጃ በመዋቅር እየተሠራ ነው ያሉት ዳይሬክተሯ በዩኒቨርሲቲው ካሉ ሴት መምህራንና የአስተዳደር ሠራተኞች ቁጥር አኳያ በሚፈለገው ልክ አለመሠራቱን ተናግረዋል፡፡ በመሆኑም ውይይቱ በመመሪያዎች፣ አሠራሮችና በራሳቸው በሴቶች በኩል ያሉ ችግሮች ተለይተው በሚፈቱበት ሁኔታ ቀጣይ ሥራዎችን ለማከናወን የሚረዳ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በውይይቱ ወቅት የሴቶች ጉዳይ በነጭ ሪባን ቀን፣ በዓለም የሴቶች ቀን ክብረ በዓልና በሥልጠና ብቻ የሚፈታ አለመሆኑ የተገለጸ ሲሆን ሴቶች ጉዳዮቻቸውን በነፃነት በማንሳት የገጠማቸውን ችግሮች እርስ በእርስ በመደጋገፍ መፍታትና ከአቅም በላይ ከሆነ ለሚመለከተው ክፍል በማድረስ ለመፍታት የሚያስችሉ ሃሳቦችም ተነስተዋል፡፡ በውይየቱ ለተነሱ ጥያቄዎችና አስተያየቶች የሚመለከታቸው አካላት ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት