Print

 አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ከግብርና ሳይንስ፣ ከተፈጥሮና ቀመር ሳይንስ እና ከሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጆች ጋር በመተባበር 8ኛውን ሳይንስ ለዘላቂ ልማት ዓውደ ጥናት ከመጋቢት 30 - ሚያዝያ 01/2014 ዓ/ም አካሂዷል፡፡ በዓውደ ጥናቱ ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች የተወጣጡ በግብርና፣ ጤና እና የተፈጥሮ ሳይንስ ዘርፎች የተዘጋጁ 58 ጥናታዊ ጽሑፎች ቀርበዋል፡፡ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የዩኒቨርሲቲው የምርምርና ማኅበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዝደንት ተ/ፕ በኃይሉ መርደኪዮስ ምርምር ዕውቀት ለማስፋትና ለተለያዩ ችግሮች መፍትሔ ለማፈላለግ በሙከራዎች፣ በመስክ ላይ ጥናት እና በምልከታ መረጃን ማግኘት፣ ማጠናቀርና መተንተን የሚያካትት መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ሂደቱም ሳይንሳዊ ቅቡልነት ያለውና የምርምር ሥነ ምግባርን የተከተለ መሆን ይገባዋል ያሉት ም/ፕሬዝደንቱ የምርምር ውጤቶች ትርጉም ባለው መልኩ ወርደው ለማኅበረሰብ አገልግሎትና ቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲውሉ ይጠበቃል ብለዋል፡፡

የአካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዝደንትና የፕሬዝደንቱ ተወካይ ዶ/ር ዓለማየሁ ጩፋሞ በመክፈቻ ንግግራቸው አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ምርምርን እንደ ማቀጣጠያ መሣሪያ ተጠቅሞ የሀገራዊ ኅዳሴ ግብን እውን ለማድረግ ብሎም የምርምር ዩኒቨርሲቲ ሆኖ ለመመረጡ ብቁነቱን ሊያረጋግጡ የሚችሉ ሥራዎችን እየሠራ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡ ዓመታዊ የምርምር ዓውደ ጥናት ጊዜውን ጠብቆ መከናወኑ ዩኒቨርሲቲው ተመራማሪዎችን፣ ባለሙያዎችንና ፖሊሲ አውጪዎችን የሚያገናኙ ቀጣይነት ያላቸው ሳይንሳዊ መድረኮችን በማዘጋጀት ሳይንስን ለዘላቂ ልማት ለማዋልና የማኅበረሰቡን ችግሮች ለመምፍታት ያለውን ቁርጠኝነት ያሳያል ብለዋል፡፡

የምርምር ዳይሬክቶሬት ቺፍ ኤክስኪዩቲቭ ዳይሬክተር ዶ/ር ተስፋዬ ሀ/ማርያም በዩኒቨርሲቲውና በአካባቢው ምርምሮችን ለመሥራት ያሉ ምቹ ሁኔታዎችን ለታዳሚዎች ሲገልጹ ዩኒቨርሲቲው የጋራ ፕሮጀክቶችን በመሥራት ልምድ ያካበተ መሆኑን፣ አካባቢው በደጋ ፍራፍሬና አትክልት፣ በእንሰት፣ በተዘነጉ የቆላማ በሽታዎች እንዲሁም በመሬት መራቆትና መንሸራተት ላይ ለማጥናት የሚሆን የተፈጥሮ ሀብትና መነሻ ችግሮች ያሉ መሆኑን ጠቅሰው በጋራ ለመሥራት ፍላጎቱ ላለው ሁሉ ዩኒቨርሲቲው ክፍት ነው ብለዋል፡፡

የሕፃናት ሥነ ምግብ ስፔሺያሊስት፣ በጂማ ዩኒቨርሲቲ ነባር ተመራማሪና የፍኖት ፕሮጀክት ዳይሬክተር ፕ/ር ጽኑኤል ንጋቱ ‹‹Nurturing Research Partnership and Translation›› በሚል ርዕስ የምርምር ልምዳቸውን መነሻ አድርገው ባስተላለፉት ቁልፍ መልዕክት ያደጉት ሀገራት በ3ኛ ዲግሪ ትምህርትና ሳይንሳዊ ምርምሮች የገፉ መሆኑ በኑሮ ሁኔታና በዕድሜ ጣሪያ የተሻሉ እንዲሆኑ አስተዋፅኦ ማበርከቱን ተናግረዋል፡፡ በሀገራችንም ሳይንስ ልማትን የሚመራና የሚያፋጥን መሆን ቢገባውም በተለይም በክሊኒካል ምርምር ዘርፍ ጥቂት ተመራማሪዎች ብቻ የሚገኙ በመሆኑ በጋራ የሚሠሩ ምርምሮችን ማስፋት አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

የጋራ ምርምሮችን ለማካሄድ የሳይንስ አቅራቢና ተጠቃሚ ፍላጎት፣ አብሮ የመሥራት ዕድል እና ብቃት አስፈላጊ ግብዓቶች ናቸው ያሉት ፕ/ር ጽኑኤል መሠረታዊ የምርምር፣ የአመራር፣ የድርድርና የግጭት አፈታት ክሂሎቶች ወሳኝ ናቸው ብለዋል፡፡ በተጨማሪም በምርምር ቡድኑ በሙያ፣ በአካባቢና በአመለካከት የተለያዩ አባላትን ማሳተፍ የተለያዩ ሃሳቦችን ለማንሸራሸርና የምርምር ጥራትን ለማሳደግ ጠቃሚ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በፊዚክስ ትምህርት ዘርፍ ተባባሪ ፕሮፌሰር የሆኑት ሌላኛው የቁልፍ ንግግር አቅራቢ ዶ/ር ጥላሁን ተስፋዬ የሳይንስ ምንነት፣ ግልጋሎት፣ ከዘላቂ ልማት ጋር ያለው ትስስርና መሰል ጉዳዮችን ዳስሰዋል፡፡ የሳይንስ ዕሴቶች ለሁሉም መስኮች የጋራ መሆናቸውን የጠቀሱት ዶ/ር ጥላሁን ሳይንስን መማር በየትኛውም የሕይወት መስክ በጎ አመለካከቶችን ለመቅረጽ የሚያስችል በመሆኑ በሳይንስ የበለፀገን ማኅበረሰብ በቀላሉ መጠምዘዝና መምራት የማይቻል ነው ብለዋል፡፡ ማኅበረሰቡን፣ ኢኮኖሚውንና የተፈጥሮ ሀብትን በዘላቂነት ለማልማትና ትውልድ የሚሻገር መሠረት ለመጣል ሳይንስን መማር፣ በምርምር ማበልጸግና በሳይንስ መኖር እንደሚያስፈልግ ዶ/ር ጥላሁን ተናግረዋል፡፡

በዓውደ ጥናቱ ከቀረቡ የምርምር ጽሑፎች መካከል በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ግብርና ሳይንስ ኮሌጅ ፕሮፌሰር ይስሃቅ ከቸሮ ‹‹Blood Metabolites, Milk Yield and Body Condition Score as Markers for the Nutritional Status of Ranging Dairy Cows: the case of the South Ethiopian Rift Valley›› በሚል ርዕስ ያቀረቡት ጥናት አንዱ ነው፡፡ ፕ/ር ይስሃቅ በጥናታዊ ጽሑፋቸው እንዳመለከቱት እንደ ኢትዮጵያ ባሉ በርካታ ሞቃታማ ሀገራት ከፍተኛ የከብት ቁጥር ቢኖርም በአብዛኛው በወቅታዊ የተፈጥሮ ግጦሽ፣ ሣርና የሰብል ቃርሚያ ላይ የተመሠረተ አመጋገብና ባህላዊ አያያዝ የሚከተሉ በመሆኑ የወተት ምርቱ እጅግ ዝቅተኛ ነው፡፡ ግጦሹ በአግባቡ ባለመመራቱ ለመሬት መራቆትና የአፈር መሸርሸር የሚዳርግ በመሆኑ በደረቅ ወቅቶች በወተት ላሞች ላይ ተፅዕኖ ያሳድራል፡፡ ችግሩን ለመቅረፍ የንጥረ ምግብ እጥረት ልየታ ጥናት ማድረግ አስፈላጊ በመሆኑ የከብቶችን አመጋገብ በማስተካከል የወተት ምርቱን ለማሻሻል የደምና የምራቅ ናሙና በመውሰድ እንዲሁም የከብቶቹን አካላዊ ሁኔታና የወተት አሰጣጥ በመገምገም ጥናቱ ተሠርቷል፡፡

የጥናቱ ውጤቱ አካባቢያዊ የአየር ንብረትና ወቅቶች በከብቶቹ አመጋገብና በሚያገኟቸው ንጥረ ነገሮች ላይ ልዩነት የሚፈጥር መሆኑ በወተት ምርቱ ላይ ተፅዕኖ እንደሚያሳድር ያሳየ ነው፡፡ በመሆኑም እንደየ አካባቢውና እንደየ ወቅቱ ለከብቶች አመጋገብ የተለያዩ ዘዴዎችን በመጠቀም የወተት ምርታማነትን ማሻሻል እንደሚቻል አጥኚው ጠቁመዋል፡፡

ሌላኛው ጥናት አቅራቢ የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ኬሚስትሪ ዲፓርትመንት መምህርና ተመራማሪ ዶ/ር ዘላለም ይብራልኝ ‹‹Isolation of New Cytotoxic Flavonoid from the Stem Bark of Erythrina cafra›› በተሰኘው ጥናታቸው በሳይንሳዊ መጠሪያው ‹‹Erythrina cafra›› ከተሰኘው ዛፍ የግንድ ቅርፊት አዲስ ውሕድ ንጥረ ነገሮችን መለየታቸውን ገልጸዋል፡፡ ዛፉ በደቡብ ምሥራቅ አፍሪካ አካባቢዎች ሀገር በቀልና በስፋት የሚገኝ ሲሆን ቅርፊቱን ቲቢ፣ የመተንፈሻ አካላት ኢንፌክሽን፣ ቁስለት፣ የአንጓ ብግነት (arthritis)፣ የጥርስ ሕመም፣ የቅጠሉን ጭማቂ የጆሮ ሕመም እንዲሁም የሥሩን መረቅ ወለምታ ለማከም ይጠቀሙበታል፡፡

በጥናቱ የተክሉን የግንድ ቅርፊት በመሰብሰብ፣ በማድረቅና በመፍጨት የተለያዩ የልየታ ዘዴዎችን ተጠቅመው ውሕዶችን በመለየት መዋቅራዊ ትንተና አድርገዋል፡፡ በዚህም 7 አዳዲስ ውሕዶችን ለማግኘት የተቻለ ሲሆን ተክሉ በ‹flavonoid› ውሕዶች የበለጸገ በመሆኑ በቅርፊቱ ብቻ ሳይሆን በሁሉም የተክሉ ክፍሎች ተጨማሪ ጥናት ሊደረግበት እንደሚገባ በጥናታቸው መደምደሚያ ጠቁመዋል፡፡

በጂማ ዩኒቨርሲቲ የማኅበረሰብ ጤና ፋከልቲ መምህርና ተመራማሪ አቶ አብርሃም ታምራት የቀረበው ‹‹Knowledge, Attitude and Breastfeeding Self-efficacy among Mothers with Infant and Young Child (0-24 months): Baseline Data of Cluster-Randomized Control Trials in Maji Woreda, West Omo Zone, Southwest

Region, Ethiopia›› ጥናት በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ከፊል አርብቶ አደር አካባቢ ማኅበረሰብ ጨቅላ እና እስከ 2 ዓመት ዕድሜ የሚሆኑ ሕፃናት ያላቸው እናቶች የጡት ማጥባት ዕውቀት፣ አመለካከትና ልምዳቸውን የሚዳስስ ነው፡፡

በጥናታዊ ጽሑፉ እንደተመለከተው ጡት ማጥባት ለጨቅላ ሕፃትም ሆነ ለአጥቢ እናቶች በርካታ ጠቀሜታዎች ያሉት መሆኑን የሚደግፉ ጠንካራ ማስረጃዎች ቢኖሩም በዓለም አቀፍ ደረጃ በተለይም በኢትዮጵያ እምብዛም ወደ ማኅበረሰቡ አልሰረጹም፡፡ የዕውቀት ማነስ፣ አሉታዊ አመለካከቶች፣ አሉታዊ ማኅበራዊና ባህላዊ ልማዶች እና ሌሎችም ምክንያቶች የጡት ማጥባት ልምድ ዝቅተኛ እንዲሆን አድርገዋል፡፡

በዓውደ ጥናቱ የኢትዮጵያ ባዮዳይቨርሲቲ ኢንስቲትዩት ም/ዳይሬክተርና የአ/ም/ዩ የቀድሞ ፕሬዝደንት ዶ/ር ፈለቀ ወልደየስ፣ የኢትዮጵያ የደን ምርምር ኢንስቲትዩት ም/ዳይሬክተርና የአ/ም/ዩ የቀድሞ አካዳሚክ ጉ/ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር አጌና አንጁሎ፣ በኢትዮጰያ ባዮቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት የኢንደስትሪያል ባዮቴክኖሎጂ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተርና የቀድሞ የአ/ም/ዩ የምርምርና ማኅበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ፋንታሁን ወ/ሰንበትን ጨምሮ ከአዲስ አበባ፣ ጂማ፣ ባሕር ዳር፣ ኮተቤ ሜትሮፖሊታን፣ ጎንደር፣ አዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ፣ ወለጋ፣ ደ/ማርቆስ፣ መቱ፣ ሐረማያ፣ አምቦ፣ ሰላሌ፣ ሚዛን ቴፒ፣ ወልቂጤ፣ ወልዲያ፣ ድሬዳዋ፣ ደብረ ታቦር፣ መዳ ወላቡ፣ ሀዋሳ፣ ዲላ፣ ወላይታ ሶዶ፣ ዋቸሞ እና አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲዎች ተመራማሪዎችና ተሳታፊዎች ተገኝተዋል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት