የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ኢንፎክን የመጻሕፍት እና የመረጃ ማዕከል ‹‹የብዕር ጥበብ›› አስተዋይ ወጣት ለኢትዮጵያ አንድነት በሚል ርዕስ ሚያዝያ 8/2014 ዓ/ም የኪነ ጥበብ ፕሮግራም አካሂዷል፡፡ በፕሮግራሙ ጋዜጠኛና ደራሲ ዘነበ ወላ፣ ደራሲ መሐመድ አሊ (ቡርሃን አዲስ) እና የጋሞ አባቶች በተጋባዥ እንግድነት ተገኝተዋል፡፡ ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ በሰው ልጆች የእድገት ሂደት ወጣትነት ከፍተኛ የፈጠራ፣ የጥበብና የማኅበራዊ እሴት ሥራዎች አቅም የሚያድግበትና የሚፈፀምበት የሕይወት ምዕራፍ መሆኑን ተናግረው ወጣቱን በጥበብና በግብረ ገብ መገንባት ለአንድ ሀገር ሰላም፣ ሀገራዊ አንድነትና ሁለንተናዊ እድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለው ብለዋል፡፡ በተለይ በአሁኑ ሰዓት በሀገራችን እየተፈጠሩ ያሉት ክስተቶች የኢትዮጵያን አንድነት እና የሕዝቡን ዘመናት የተሻገረ አብሮነትና ወንድማማችነት እንዳይጎዱ በማንበብና ጥበብን በማሳደግ የሚገኝ የአስተሳሰብ ብስለት ወጣቱ ንቁና በአላስፈላጊ ቡድኖች በቀላሉ የማይመራ እንዲሆን እንደሚረዳው ፕሬዝደንቱ ገልጸዋል፡፡ መሰል የሥነ ጽሑፍ ዝግጅቶችም ወጣቱ እርስ በእርሱ፣ የተሻለ ልምድ ካላቸውና ከማኅበረሰቡ ልምዶችንና አስተውሎቶችን በመጋራት የሚማማርበት ነው ብለዋል፡፡

ጋዜጠኛና ደራሲ ዘነበ ወላ ለተማሪዎች ባስተላለፈው መልዕክት ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በርካታ ኢንደስትሪዎችን የሚያንቃሳቅስና በሚሊዮኖች ለሚቆጠሩ ዜጎች የሥራ ዕድል የሚፈጥር የሀገራችን ትልቅ በረከት መሆኑን ጠቅሶ ይህን እውን ለማድረግ በጽናትና በአንድነት በመቆም በጉልበትና በዕውቀት ሁሉም የድርሻውን መወጣት እንደሚገባው ተናግሯል፡፡
ደራሲ ዘነበ ሥነ ጽሑፍ የሚያበረክተውን ፋይዳ ሲገልጽ በዓባይ ውኃ ላይ ግብጾች 2,200 መጻሕፍት፣ ከ10,000 በላይ ምሳሌያዊ ንግግሮችና 1,500 ጥናታዊ ጽሑፎች አሏቸው ብሏል፡፡ ተማሪዎች ተመርቀው ወደ ሥራ ዓለም ሲቀላቀሉ በየተሰማሩበት ዘርፍ ሁሉ በአስተዋይነት፣ በጥበብና የማንበብ ልምድን በማዳበር ለሀገራቸውም ሆነ ለዓለም የየራሳቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱም መልዕክቱን አስተላፏል፡፡ 

ደራሲ መሐመድ አሊ (ቡርሃን አዲስ) በበኩሉ ሃይማኖት፣ ባህልና ቤተሰብ ሀገራት ለረዥም ዓመታት ጠንካራ ሆነው የቆዩባቸው ዕሴቶች መሆናቸውን ተናግሮ በአሁኑ ሰዓት ግን በተለይ በተማረው ማኅበረሰብ አካባቢ እነዚህ እሴቶች የኋላቀርነት መገለጫ ተደርገው እየታዩ ነው ብሏል፡፡ እሴቶቹ የማኅበረሰብ ሞራልና ምግባርን የሚጠብቁ፣ ለሌሎች መኖርና ኃላፊነት መውሰድን የሚያስተምሩ እንዲሁም ማኅበረሰቡ ራሱን ሉዓላዊ አድርጎ እንዲቆይ የሚያስችሉ መሆናቸውን ተናግሯል፡፡

የተዛነፈ አመለካከትና ዕይታ ያለው ማኅበረሰብ የተቃና ሀገር ሊኖረው አይችልም ያለው ደራሲ መሐመድ መሰል ዝግጅቶች በወጣቶች መሰናዳታቸው ሀገርን የሚረከብና አንድነቷን የሚያስጠብቅ ትውልድ እንዳለ ተስፋ የሚሰጥ እንዲሁም ወጣቶች ስለ ሀገራቸው ያገባናል እንዲሉና ከልዩነታችን ይልቅ አንድ የሚያደርገንን ነገር በማጉላት ለመጪው ትውልድ መልካም ተሞክሮዎችን ማስተላለፍ እንድንችል የሚረዳን ነው ብሏል፡፡

የጋሞ አባቶች ተወካይ አቶ ሰዲቃ ስሜ ወጣቶች በሃይማኖት፣ በዘር፣ በቀለምና በብሔር ከመጋጨት ይልቅ ከጥላቻ ንግግሮች በመቆጠብ ሀገራዊ አንድነትን ለመገንባት እንዲሠሩና የጀመሩትን መልካም ተሞክሮ አጠናክረው እንዲቀጥሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

የኢንፎክን የመጻሕፍት እና የመረጃ ማዕከል ሰብሳቢ ተማሪ ኢብራሂም ካሴ እንደገለጸው ፕሮግራሙ በዋናነት ወጣቶች ላይ ትኩረት ያደረገ ሲሆን የከፍተኛ ትምህርት ተቋም እንደ መሆኑ ተማሪዎች ከትምህርታቸው ጎን ለጎን ሀገራዊና ሌሎች ይዘቶች ያላቸው አስተሳሰቦች ላይ ትኩረት በማድረግ አስተዋይ ወጣት እንዲሆኑ ያለመ ነው፡፡

እንደዚህ ዓይነት መድረኮች መዘጋጀታቸው ተማሪዎች እንደ አካዳሚክ ትምህርታቸው ሁሉ በንባብ ዕውቀታቸውን በማዳበር አስተሳሰባቸውን ይገነባል ብሏል፡፡
በዕለቱ ግጥሞች፣ ቴአትር፣ ሥነ ጽሑፍ እና በከተማው ኪነት ባንድ የተለያዩ ጣዕመ ዜማዎችና ባህላዊ ጭፈራዎች ቀርበዋል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት