የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የተፈጥሮና ቀመር ሳይንስ ኮሌጅ የማኅበረሰብ አገልግሎት ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ለባልታ 2ኛ ደረጃ ት/ቤት ለመማር ማስተማር ሥራ የሚውሉ የባዮሎጂ፣ የኬሚስትሪና የፊዚክስ ቤተ-ሙከራ ኬሚካሎችና ቁሳቁሶችን ሚያዝያ 8/2014 ዓ/ም ድጋፍ አድርጓል፡፡ ድጋፉ በገንዘብ ሲተመን 130,000 (አንድ መቶ ሠላሳ ሺህ) ብር የሚያወጣ መሆኑ ተገልጿል፡፡

የተፈጥሮና ቀመር ሳይንስ ኮሌጅ ዲን ዶ/ር ቴዎድሮስ ብርሃኑ የማኅበረሰብ አገልግሎት ለዩኒቨርሲቲዎች ከተሰጡ ተልዕኮዎች አንዱ መሆኑን ገልጸው በጋሞ ዞን ውስጥ ያሉ የ2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ክፍተቶች ያሉባቸውና ደረጃቸውን ያልጠበቁ በመሆናቸው እነርሱን የመደገፍ ኃላፊነት አለብን ብለዋል፡፡ ስለሆነም የ2ኛ ደረጃ ት/ቤቶች ቤተ-ሙከራዎችን በቁሳቁስ የማደራጀትና ሥልጠና የመስጠት ሥራ እያከናወኑ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ሰፊ ድጋፎችን ለማድረግ የአቅም ውስንነት መኖሩን የተናገሩት ዲኑ የዩኒቨርሲቲውን ሀብትና ትምህርት ቤቶቹ ጋ ያለውን ክፍተት በመለየት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በጋራ መሥራት እንደሚያስፈልግም ገልጸዋል፡፡  ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የኮሌጁ የማኅበረሰብ አገልገሎት አስተባባሪ ዶ/ር ተስፋዬ ገ/ማርያም በበኩላቸው ባልታ 2ኛ ደረጃ ት/ቤት የትምህርት ግብዓት እጥረት ያለበት በመሆኑና ት/ቤቱ ለዩኒቨርሲቲው ባቀረበው ጥያቄ መሠረት ድጋፉ መደረጉን ተናግረው ከቁሳቁስ ድጋፉ ባሻገር ሥልጠና መሰጠቱን ገልጸዋል፡፡ መሰል ድጋፎች በጋሞ ዞን ውስጥ ላሉ የአቅም ማነስ የሚታይባቸው 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የሚደረጉ መሆኑን የጠቀሱት ዶ/ር ተስፋዬ ድጋፎቹ የተጎዱ ት/ቤቶችን ለማደራጀትና የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖራቸው ተናግረዋል፡፡

የባልታ 2ኛ ደረጃ ት/ቤት ርዕሰ መምህር አቶ አረጋ አቦዬ ዩኒቨርሲቲው ከዚህ ቀደምም ተመሳሳይ ድጋፍ ማድረጉን አስታውሰው በየዓመቱ ከሚጨምረው የተማሪዎች ቁጥር ጋር የሚመጣጠን ግብዓት አስፈላጊ በመሆኑ የመማር ማስተማር ሂደቱን ለማሻሻል የዩኒቨርሲቲው ድጋፍ ከፍተኛ ሚና እንዳለው ገልጸዋል፡፡

የጋሞ ዞን ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ኃላፊ አቶ ሙናዬ ሞሶሎ ‹‹የባልታ ተወላጆችና ደጋፊዎች የትምህርት መርጃ መሳሪያ አቅራቢና አፈላላጊ ማኅበር›› አባል መሆናቸውንና በበጎ ፈቃደኝነት የባልታ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ክፍተቶችን ለመሸፈን እየሠሩ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ በተለይ የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች ውጤት ላይ ለውጥ ሊያመጡ የሚችሉ ግብዓቶች ላይ ለመሥራትና ሌሎች ትምህርት ቤቶች ላይም ያሉትን ችግሮች ለመቅረፍ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ዕቅድ ይዘን እየሠራን ነው ያሉት አቶ ሙናዬ ስለተደረገው ድጋፍ ዩኒቨርሲቲውን አመስግነዋል፡፡

አሠልጣኝ መምህራን እንደገለጹት በቤተ ሙከራ አገልግሎትና አጠቃቀም ዙሪያ መምህራን ተማሪዎችን እንዴት ማሠራት እንደሚችሉና የመረጃ አወሳሰድ ሥልጠና መስጠታቸውን ተናግረዋል፡፡

በፕሮግራሙ የጋሞ ዞን ትምህርት መምሪያ ኃላፊ፣ የጋሞ ዞን ባሕልና ቱሪዝም መምሪያ ኃላፊ፣ የከምባ ዙሪያ ወረዳ አስተዳዳሪ፣ የተፈጥሮና ቀመር ሳይንስ ኮሌጅ የማኅበረሰብ አገልግሎት አስተባባሪ፣ መምህራን፣ የወረዳው ተጋባዥ እንግዶችና ሌሎችም ተሳትፈዋል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት