አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩትነት ከተቋቋመበት ከ1979 ዓ/ም ጀምሮ ለአርባ ምንጭ ከተማ፣ ለጋሞ ዞንና የዞኑ ወረዳዎች፣ አጎራባች ዞኖችና ልዩ ወረዳዎች እንዲሁም ከተማ አስተዳደሮች ከመደበኛው መማር ማስተማርና ምርምር ጎን ለጎን በማኀበረሰብ አገልግሎት ዘርፍ እያገለገለ ቆይቷል፡፡

አርባ ምንጭ ከተማንም “የዩኒቨርሲቲ ከተማ” ተብሎ ሊጠራ እስከሚችልበት ድረስ እየተጠናቀቀ የሚገኘውን የሪፈራልና ማስተማሪያ ሆስፒታል ካምፓስን ጨምሮ 6 ካምፓሶች በመመሥረት በከተማው ዕድገት ላይ አዎንታዊ ሚና መጫወቱ ይታወቃል፡፡ የተለያዩ ተቋማትን፣ ቀበሌያትንና ግለሰቦችን በቁሳቁስ፣ በሥልጠና፣ በነጻ የትምህርት ዕድል፣ በሕክምናና ሌሎች ድጋፎች እያደረገ እያገለገለም ይገኛል፡፡

ይሁን እንጂ ከመጋቢት 28/2014 ዓ/ም ወዲህ የአርባ ምንጭ ከተማ አስተዳደር ዩኒቨርሲቲው ላለፉት 34 ዓመታት እያስተዳደረ የሚገኘውን ከዩኒቨርሲቲው ዋና ግቢ ከተማሪዎች መግቢያ በር ትንሽ ወረድ ብሎ ከአውራ ጎዳናው ባሻገር የሚገኘውን የምርምርና የሠርቶ ማሳያ ቦታ ዩኒቨርሲቲው ምንም መረጃ ባልደረሰውና ምንም ዓይነት ተግባቦት ባልተደረገበት ሁኔታ በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ገቢ ማስገኛ ድርጅት አማካኝነት ሥራ ላይ የነበሩ ማኔጀሩ እና ሠራተኞች ሥራ ላይ ከነበረው የእርሻ መኪና (ትራክተር) ጋር በፖሊስ ቁጥጥር ሥር እንዲውሉ ተደርጓል፡፡ በወቅቱ በደረሰው መረጃ በካውንስል ስብሰባ ላይ የነበሩ የማኔጅመንት አባላት በጉዳዩ ድንገተኛነት በመደናገጥ ስብሰባ አቋርጠው ተፈጠረ ወደ ተባለው ጉዳይ አምርተዋል፡፡ በመቀጠልም ከሚመለከታቸው ከከተማ አስተዳደሩና ከዞኑ አመራር አካላት ጋር በስልክና በአካል በተደረገው ውይይት የተፈጠረው ጉዳይ ስህተት መሆኑ የተገለጸ ሲሆን በተለይ ዞኑ ጉዳዩን ጭራሽ የማያውቀው መሆኑን በመግለጽ ስህተቱ እንዲታረም እንደሚደረግ መግባባት ላይ ስለተደረሰ ጉዳዩ በቀላሉ የሚታለፍ ባይሆንም ከሰው ስህተት አይጠፋም በሚል ይቅርታ ታልፎ ነበር፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ ቀጥሎም በአርባ ምንጭ ከተማ ማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎት የመሬት ድልድላ እየተደረገ በመገኘቱ የዩኒቨርሲቲው የፀጥታና ደኅንነት ዘርፍ በቦታው በመገኘት ጉዳዩ በሕግና ደንብ መሠረት ተገቢው ተግባቦት ተደርጎ የዩኒቨርሲቲው አመራር እንዲያውቅ ባልተደረገበት ሁኔታ እየተሠራ ያለው ሕገ ወጥ ሥራ እንዲቆም ለመከላከል ባደረጉት ጥረት ያለ ፍርድ ቤት ማዘዣ የፌዴራል ተቋምን በመድፈርና ሕግ በመጣስ እንዲታሠሩ ተደርጓል፡፡ ከዚህም ቀጥሎ ዩኒቨርሲቲው እየተካሄደ ያለው ጉዳይ ሕገ ወጥ መሆኑን ከግንዛቤ ውስጥ በማስገባት ጉዳዩ በሠላማዊ መንገድ በድርድር እንዲፈታ ለማድረግ ያላሰለሰ ጥረት ሲያደርግ ቢቆይም ከከተማ አስተዳደሩና ከዞኑ ከፍተኛ አመራሮች ግን ተገቢ ምላሽ ሊሰጥና በዩኒቨርሲቲው ይዞታ መሬት ላይ ሊፈጸም እየተደረገ ያለው የመሬት ወረራ ሙከራ ሊቆም አልቻለም፡፡

ለድርድር ምንም ዕድል አለመሰጠቱ ከሁሉ በላይ አሳዛኝ ሆኗል፡፡ የስልክና የቃል መሸንገያዎችን በመጠቀም የጊዜ ማራዘሚያ ስልት ከመጠቀም ውጭ ለዩኒቨርሲቲው ጥያቄ ምላሽ የመስጠት ፍላጎት አለመኖሩን የተገነዘበው የዩኒቨርሲቲው የሕግ አገልግሎት ለጋሞ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ባቀረበው የሁከት ይወገድልኝና የፍትሃብሔር ክስ ምላሽ እንዲሰጥ የፍርድ ቤት መጥሪያና ትዕዛዝ ለአርባ ምንጭ ከተማ ማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎት እንዲደርስ ተደርጓል፡፡ በተለይም ፍ/ቤቱ በሁከት ይወገድልኝ ክስ ለከተማው ማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎት ባስተላለፈው እገዳ በ21/8/2014 ዓ/ም የክሱን ምላሽ እስከሚያቀርቡ ድረስ የእግድ ማዘዣ የወጣ መሆኑን በማስገንዘብ የእግድ ትዕዛዙን ለመቃወም የሚፈልግ ከሆነ ማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎቱ በ13/8/2014 ዓ/ም ከቀኑ 8፡00 ምላሽ ይዞ እንዲቀርብ ተብሎ የታዘዘበትን የፍርድ ቤት ትዕዛዝ በ11/8/2014 ዓ/ም ተቀብሎ ባለበት ሚያዝያ 13/2014 ዓ/ም ከማለዳው ጀምሮ የፍ/ቤቱን እገዳ በመጣስ በዩኒቨርሲቲው የምርምርና የሠርቶ ማሳያ መሬት ላይ የድልደላ ሥራና ከዚያም አልፎ በግሬደር የመሬት ጠረጋ ሥራ እየሠራ መሆኑ ስለተገለፀ ይህንን በሕግ አግባብ እንዲቆም የተጠየቀ ሆኖ ሳላ በመሬቱ ላይ ባለው የዩኒቨርሲቲው በብዙ ሚሊዮን በሚገመት ሀብት ላይ ጉዳት እንዳይደርስበት በማሳብ የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛና መካከለኛ አመራሮች በቦታው ላይ ምልከታ ለማካሄድ ሊገኙ ችለዋል፡፡

በዚህም ጊዜ በቦታው በስምሪት ላይ የነበሩ ፖሊሶች ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ ለምን ሁከት ለመፍጠር መጣችሁ በሚል የዩኒቨርሲቲውን ፕሬዝደንት፣ የቢዝነስና ልማት ም/ፕሬዝደንት እና የአስ/ጉዳዮች ም/ፕሬዝደንት ተወካይ፣ የአካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዝደንት፣ የአርባ ምንጭ ውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ሳይንቲፊክ ዳይሬክተርና የዩኒቨርሲቲውን የሕግ አገልግሎት ዳይሬክተር በቁጥጥር ውስጥ አድርገው ለእስርና እንግልት እንዲሁም በመንግሥት ሥራ ላይ ከፍተኛ በደል እንዲደርስ አድርጓል፡፡ የፍርድ ቤት የእገዳ ትዕዛዙን የማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎቱ በቀን 11/8/2014 ዓ/ም ፈርሞ ቢወስድም የፀጥታ ዘርፉ ግን የእገዳ ደብዳቤውን አላመጣችሁም ብሎ ነው ኃላፊዎቹን ለማሰር የተጣደፈው፡፡ የዩኒቨርሲቲውን አመራር ማሰሩ ለጉዳዩ እንደ ስኬትና መፍትሄ ከተወሰደ ሁሉም አመራሮች ለእስሩ ፈቃደኛ ቢሆኑም የእስሩ ድራማ ያነጣጠረው በተወሰኑ ኃላፊዎች ላይ ብቻ ያተኮረ ስለነበረ አብረው የሄዱትንም ቢሆን ያልተፈለጉት ወዲያው እንዲለቀቁ ተደርገዋል፡፡ ይህም የፀጥታ ዘርፉ ተገቢ ያልሆነና በግለሰቦች ላይ ያነጣጠረ ተልዕኮ እንደነበረው አመላካች ነበር፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በአሁኑ ሰዓት በሀገሪቱ ካሉት 8 የምርምር ዩኒቨርሲቲዎች አንዱ ሆኖ ሊመረጥ የቻለው አሁናዊ የምርምር ላቦራቶሪዎች፣ የምሁራንና የምርምር ማዕከላት አደረጃጀት እንዲሁም ዩኒቨርሲቲው ለወደ ፊት ምርምርን ለማስፋፋት ያለውን አቅምና ግብዓት ከግንዛቤ ውስጥ በማስገባት መሆኑ እሙን ነው፡፡ ዩኒቨርሲቲው በአቅራቢያው ያለውን መሬት ግንባታዎችን ሳይሠራበት እያቆየ ያለው ለወደ ፊቱ ለአካባቢውና ለሀገር የሚጠቅም የምርምር ሥራ ለመሥራት አስቦ እንጂ እንደ ከተማ አስተዳደሩ ስሌት መሬቱን ለመጠቀም ፍላጎት ሳይኖረው ወይም አቅም አንሶት አለመሆኑን ዩኒቨርሲቲው በጽኑ ይገነዘባል፡፡ በአሁኑ ሰዓትም ቢሆን በመሬቱ ላይ የውሃና የአፈር ምርምሮች፣ የሚቲዎሮሎጂ መረጃ ጣቢያዎች፣ የግብርና ዘርፍ ምርምሮች እና ሌሎችም እየተካሄዱ የሚገኙበት ነው፡፡ ለአብነትም ከግብርና ዘርፍ በሸንኮራ አገዳ፣ በቡና፣ በሀለኮ፣ በጥጥ፣ በዓሳ፣ በስንዴ፣ በውሃ አጠቃቀም፣ በመስኖ እና ሌሎችም ላይ ተከታታይ የሆኑ ምርምሮች በሠርቶ ማሳያ ተደግፈው እየተሠሩ ያሉ መሆኑ ይታወቃል፡፡

ከዩኒቨርሲቲው ሊወሰድ የታሰበው የምርምርና የሠርቶ ማሳያ መሬት በውስጡ ኦክሲዴሽን ፖንድ (Oxidation Pond)፣ 5 መቶ ሜትር የኢሪጌሽን ካናል፣ የዓሳ እርባታና ምርምር ገንዳ፣ የሚቲዎሮሎጂ መተንበያ ጣቢያ፣ የዩኒቨርሲቲው ትልቁ የችግኝ ጣቢያ፣ የሀለኮና የቡና ምርምር ጣቢያ፣ የሶላር ፓኔል እና ሌሎችም ሀብቶች የሚገኙበት ሲሆን መሬቱ ለወደ ፊቱም ከምርምር ጋር የተገናኙ ብዙ ጉዳዮች የሚሠሩበት ቦታ ነው፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ይህ የምርምርና የሠርቶ ማሳያ መሬት በአሁኑ ሰዓት እንደ ምርምር ዩኒቨርሲቲ ለመቀጠል የሕልውናው ጉዳይ እንደሆነ ያምናል፡፡ ዩኒቨርሲቲው ምንም እንኳን በከተማ አስተዳደሩም ሆነ በዞኑ የሚደረጉ የልማትና የዕድገት ሥራዎችን እየደገፈ ያለ ሲሆን ከዚህ በኋላም በድጋፉና በማበረታታቱ የሚቀጥል ሆኖ ሳለ የተቋሙን ሕልውና አደጋ ላይ የሚጥል ውሳኔ መተላለፉና በተለይም በዩኒቨርሲቲው ሠራተኞች፣ ከፍተኛና መካከለኛ አመራሮች ላይ የተደረገው ሕገ ወጥ፣ ኢ-ሞራላዊና ኢ-ፍትሓዊ እስርና እንግልት እንዲሁም በመንግሥት ሥራና ሀብት ላይ የተቃጠው ኃላፊነት የጎደለው ተግባር የዩኒቨርሲቲውን ማኅበረሰብ በእጅጉ ያስቆጣና ያሳዘነ መሆኑን ይገልጻል፡፡

በአሁኑ ሰዓት እንደ ቀላል መሬት መውሰድ ብቻ የመሰለው ተግባር በአጭሩ ባይቆም መሠረታዊ የልማትና የሥራ ዕድል ማጣት የሚያስከትል መሆኑን ከግንዛቤ ውስጥ በማስገባት “ዩኒቨርሲቲው መሬቱን አላለማም፤ እየተጠቀመው አይደለም” በሚል በተዛባ አመለካከት መሬቱን በሕገ ወጥ መንገድ ለመውሰድ እየተደረገ የሚገኘው ሙከራ ተገቢ ባለመሆኑ ዩኒቨርሲቲውና የዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ ድርጊቱን በጽኑ ይቃወማል፡፡ ስለሆነም ይህንን ውሳኔ ያሳለፈው አካል በውሳኔው ላይ ቆም ብሎ በማሰብ በአስቸኳይ እንዲያስተካክለው ዩኒቨርሲቲው ይጠይቃል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ከዚህ በኋላ የተፈጠረው ጉዳይ በሕግ አግባብ ብቻ እንዲፈታ በትኩረት የሚሠራ መሆኑን ለዩኒቨርሲቲውና ለአካባቢው ማኅበረሰብ በአጽንኦት ለማሳወቅ ይወዳል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት