የአርባ ምንጭ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ምርምርና ማኅበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት የዩኒቨርሲቲው የቀድሞ መምህር፣ ታዋቂ የፈጠራ ባለቤትና በIBM ካምፓኒ ውስጥ ተመራማሪ ከሆኑት ቺፍ አርክቴክት ዶ/ር ኮሚ ወ/ማርያም ጋር አርቲፊሻል ኢንተሊጀንስን በዘላቂ የምግብ ዋስትናና ግብርናን በማዘመን ዘዴ በመጠቀም ላይ ሚያዝያ 7/2014 ዓ/ም ኦንላይን ሴሚናር አካሂዷል፡፡

የኢንስቲትዩቱ ሳይንቲፊክ ዳይሬክተር ዶ/ር ሙሉነህ ለማ ሴሚናሩ አርቲፊሻል ኢንተሊጀንስ ቴክኖሎጂን በመጠቀም ዘላቂ የምግብ ዋስትናን በማረጋገጥ ሚሊየኖችን እንመግብ በሚል ርዕስ መከናወኑን ገልጸዋል፡፡ በሴሚናሩ የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ አንፃር ከመሬት አስተራረስ ጀምሮ ምርት ወደ ተጠቃሚው እስከሚደርስ ድረስ አርቲፊሻል ኢንተሊጀንስ ለሀገራችን አርሶ አደሮች ስለሚሰጠው ጥቅም ተወያይተናል ብለዋል፡፡ ዶ/ር ኮሚ የሚሠሩበት IBM ካምፓኒ ግዙፍና ልምድ ያለው እንደ መሆኑ በሀገራችን የአፈር ለምነትን ለማወቅና ከአፈሩ ጋር የሚስማማውን ምርት ለማምረት የዕውቀት ሽግግር ለማድረግ የሚረዳ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡ ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የኢንስቲትዩቱ ምርምርና ማኅበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ረ/ፕ አዲሱ ሙሉጌታ በበኩላቸው ውይይቱ የግብርና ምርታማነትን መጨመር፣ የሰብል በሽታዎችን መለየትና መከላከል፣ የግብርና መረጃ አሰባሰብና ትንተና እንዲሁም የገበያ ትስስርን መፍጠር በሚሉ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ማተኮሩን ተናግረዋል፡፡

ረ/ፕ አዲሱ ሴሚናሩ የዩኒቨርሲቲው መምህራን፣ የድኅረ ምረቃ ተማሪዎችና ተመራማሪዎች በዘርፉ ትኩረት አድርገው ምርምር እንዲሠሩ እንዲሁም ዶ/ር ኮሚ ከ150 በላይ የፈጠራ ሥራዎች ባለቤትና በትልቅ ተቋም ውስጥ የሚሠሩ በመሆናቸው የሁለትዮሽ ስምምነት በመፍጠር በፕሮጀክቶችና በመማር ማስተማር ዘርፍ በጋራ ለመሥራት ያለመ ነው ብለዋል፡፡

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ አርቲፊሻል ኢንተሊጀንስ ምርምር ማዕከል አስተባባሪና የኮምፒውቲንግና ሶፍትዌር ምኅንድስና ፋከልቲ መምህር ዶ/ር መሐመድ አበበ ሴሚናሩ የዕውቀት ሽግግር የሚደረግበትና በቀጣይም በምን ዘርፍ ላይ ምርምር መሥራት እንዳለባቸው የሚጠቁም መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በፕሮግራሙ የአርባ ምንጭ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት አመራሮች፣ የሁለቱ ኢንስቲትዩቶች መምህራን፣ የድኅረ ምረቃ ተማሪዎችና ተመራማሪዎች ተሳትፈዋል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት