የአርባ ምንጭ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ሙያ ማበልጸጊያ ማዕከል በኢንፎማይንድ ሶሉሽንስ ንዑስ የቢዝነስ ዩኒት ከሆነው ደረጃ ዶት ኮም ኃ.የተ.የግ. ድርጅት /Dereja.Com/ ጋር በመተባበር በተለያዩ የትምህርት መስኮች በ2014 ዓ/ም ለሚመረቁ ተማሪዎች ከሚያዝያ 4-7/2014 ዓ/ም የተቀጣሪነት ክሂሎት ሥልጠና ሰጥቷል፡፡

ሥልጠናው ተመራቂ ተማሪዎች ወደ ሥራ ዓለም ሲቀላቀሉ ‹‹Soft Skill›› የሚባሉትን ራስን መግለጽ፣ የጊዜ አጠቃቀም፣ በራስ የመተማመንና ሌሎች ክሂሎቶች ላይ ግንዛቤ እንዲኖራቸውና ቀጣሪው ድርጀት በሚፈልገው ልክ ብቁ ሆነው እንዲገኙ ለማድረግ ታስቦ የተዘጋጀ ነው፡፡  ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የአርባ ምንጭ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት የሙያ ማበልፀጊያ ማዕከል ማስተባበርያ ጽ/ቤት አስተባባሪ መ/ርት ስለእናት ድሪባ እንደገለጹት ዩኒቨርሲቲው ከደረጃ ዶት ኮም ጋር እ.ኤ.አ ከ2017 ዓ.ም ጀምሮ የሁለትዮሽ ስምምነት ተፈራርሞ አብሮ እየሠራ ሲሆን የተቀጣሪነት ክሂሎት ሥልጠና በየዓመቱ ይሰጣል፡፡ ድርጅቱ ተመራቂዎች በሥራ ዓለም ሊያጋጥሟቸው የሚችሉና ቀጣሪው ድርጅት ከእነሱ የሚፈልጋቸውን የጊዜ አጠቃቀም፣ ራስን የመግለጽ፣ በራስ የመተማመን እና ሌሎች በአካዳሚክ ዕውቀት የማይገኙ ክሂሎቶች ላይ ሥልጠና በመስጠት እንዲሁም ከተመረጡ ድርጅቶች ጋር በማገናኘትም የሥራ ዕድል እንዲፈጠር ያደርጋል ብለዋል፡፡

በደረጃ ዶት ኮም ሪጂናል ማኔጀርና አሠልጣኝ በእምነት ለጥይበሉ እንደተናገሩት ደረጃ ዶት ኮም እ.ኤ.አ በ2017 የተቋቋመ ድርጅት ሲሆን በቋሚነት ለአዲስ ተመራቂ ተማሪዎች ብቻ አገልግሎት የሚሰጥ ድርጅት ነው፡፡ ድርጅቱ ማስተር ካርድ ፋውንዴሽን ያንግ አፍሪካን ወርክስ/Master Card Foundation Young African Works/ ከሚባል ድርጅት ጋር ስምምነት በማድረግ እ.ኤ.አ እስከ 2020 ድረስ ከ65 ሺህ በላይ የሚሆኑ አዲስ ተመራቂ ተማሪዎችን ከቀጣሪ ካምፓኒዎች ጋር ማገናኘት ተችሏል ብለዋል፡፡

በደረጃ ዶት ኮም ረዳት አሠልጣኝ አቶ ሚካኤል ዓይናለም ደረጃ ዶት ኮም በዋነኛነት ትኩረት ሰጥቶ ከሚሠራቸው 3 ነገሮች አንዱ ደረጃ አካዳሚ አክሴሌተር ፕሮግራም መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በፕሮግራሙ በትምህርት ዓለም የማይገኙ ክሂሎቶች ላይ 2 ወር በሞጁል የተደገፈ እና ለ1 ወር በኦንላይንና በተመረጡ ትምህርት መስኮች ልምድ ካላቸው ባለሙያዎች ጋር በማገናኘት በአጠቃላይ ለ3 ወራት አሠልጥኖ የምስክር ወረቀት ይሰጣል፡፡ ዓላማውም በሀገራችን የሚታየውን የተማረ ሥራ-አጥ ቁጥር መቀነስና አዲስ ተመራቂ ተማሪዎች ልምድ ካላቸው ባለሙያዎች እኩል ችሎታ እንዳላቸው ማሳየት ነው፡፡

በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ 5ኛ ዓመት የሰርቬይንግ ምኅንድስና ተማሪ ዮሐንስ ዓለሙ ስለ ሥልጠናው በሰጠው አስተያየት ብዙ ጊዜ ዩኒቨርሲቲዎች ካስመረቁ በኋላ ተማሪዎቻቸው የደረሱበትን የማይከታተሉ መሆኑን ገልጾ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሀገሪቱ በምን መስክ የሠለጠኑ ባለሙያዎችን እንደምትፈልግ ለይተው ማስተማር አለባቸው ብሏል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት