Print

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በኢትዮጵያ የሕንድ አምባሳደር ሺሪ ሮበርት ሼትኪንቶንግ (Shri Robert Shetkintong) በተገኙበት በዩኒቨርሲቲው ከሚያስተምሩ ሕንዳውያን መምህራን ጋር ሕንድ ሀገር ከሚገኙ ተቋማት ጋር በትብብር ግንኙነት በመፍጠር ምርምር፣ ማኅበረሰብ አገልግሎትና የቴክሎጂና የፈጠራ ሥራዎችን በጋራ መሥራት በሚቻልባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ሚያዝያ 12/2014 ዓ/ም ውይይት ተካሂዷል፡፡

በውይይት መድረኩ የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር ያደረጉት የዩኒቨርሲቲው የምርምርና ማኅበረሰብ አገ/ት ም/ፕሬዝደንት ተ/ፕ በኃይሉ መርደኪዮስ አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ እንደ ሀገር ከተለዩ 8 የምርምር ዩኒቨርሲቲዎች መካከል አንዱ እንደ መሆኑ ሀገሪቱ በግብርና፣ በጤና፣ በትምህርት፣ በማዕድን ልማት፣ በቱሪዝም፣ በኢንፎርሜሽን ኮሚዩኒኬሽንና ሌሎች ዘርፎች ለማሳካት በምታደርገው ጥረት ውስጥ የበኩሉን ሚና እንዲወጣ ኃላፊነት የተሸከመ ተቋም መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ተቋሙ የተጣለበትን ሀገራዊ ኃላፊነት ለብቻው ሊወጣ አዳጋች በመሆኑ ዩኒቨርሲቲው በሀገር ውስጥም ሆነ ከሀገር ውጪ ካሉ መንግሥታዊም ሆነ መንግሥታዊ ካልሆኑ ተቋማት ጋር በትብብር ለመሥራት ዝግጁ መሆኑን የተናገሩት ተባባሪ ፕሮፌሰሩ የዕለቱ መርሃ ግብሩም በዩኒቨርሲቲው የሚሠሩ የውጭ ሀገር መምህራን ይህንን ፍላጎት ተረድተው በሀገራቸው ከሚገኙ የተለያዩ የትምህርት፣ የምርምር ተቋማትና ኢንደስተሪዎች ጋር ግንኙነት በመፍጠር በተለያዩ መስኮች የትብብር ሥራዎችን ለመሥራት የሚያስችሉ ሁኔታዎችን እንዲፈጥሩና ሃሳቦችን እንዲያፈልቁ መነሳሳትን ለመፍጠር የተዘጋጀ ነው ብለዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ በመክፈቻ ንግግራቸው ሕንድና ኢትዮጵያ በተለያዩ መስኮች በተለይ በትምህርት ዘርፍ ለረጅም ዓመታት የቆየ ጠንካራ የትብብር ግንኙነት እንዳላቸው አመልክተው ከዛሬ 40 ዓመታት ጀምሮ በርካታ ሕንዳውያን በኢትዮጵያ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤቶች ያስተምሩ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡ በሀገሪቱ ባለፉት 20 ዓመታት በነበረው ፈጣን የከፍተኛ ትምህርት መስፋፋት ጋር ተያይዞም በሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች ሊባል በሚችል ደረጃ የሕንዳውያን መምህራን ተሳትፎ ጉልህ መሆኑን የገለጹት ዶ/ር ዳምጠው ይህም በኢትዮጵያ የሰው ሀብት ልማት ውስጥ የሕንዳውያን ሚና በታሪክ የማይዘነጋ ያደረገዋል ብለዋል፡፡ አሁን ባለንበት ወቅት አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ታዋቂ የምርምር ተቋም ለመሆን እየሠራ ሲሆን ከዚህም አንፃር ሕንድና ሕንዳውያን መምህራን በፈጠራና ቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲሁም ትብብሮችን ከመፍጠር አኳያ የጎላ ሚና ይጫወታሉ ብለው እንደሚያምኑና የዕለቱ የውይይት መድረክም የጋራ ግንዛቤና መግባባት ከመፍጠር አንጻር ጉልህ ፋይዳ እንደሚኖረው ዶ/ር ዳምጠው ጠቁመዋል፡፡ ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

በኢትዮጵያ የሕንድ አምባሳደር በበኩላቸው ኢትዮጵያና ሀገራቸው እ.አ.አ በ1948 ይፋዊ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የጀመሩ መሆናቸውን ተናግረው ሁለቱ ሀገራት የጋራ ተጠቃሚነት መርህን በተከተለ መልኩ በተለያዩ መስኮች በጋራ እንደሚሠሩ ጠቁመዋል፡፡ ሁለቱ ሀገራት በትምህርት መስክ በጋራ መሥራት ከጀመሩ ረጅም ዓመታት እንዳለፉ የገለጹት አምባሳደሩ አሁንም ድረስ በርካታ ሕንዳውያን በኢትዮጵያ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እንደሚያስተምሩና በሕንድ በሚገኙ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትም በርካታ ኢትዮጵያውያን በተመቻቸላቸው ነፃ የትምህርት ዕድል ትምህርታቸውን እየተከታተሉ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡ አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በሕንድ ከሚገኙ የተለያዩ ተቋማት ጋር በትብብር የመሥራት ፍላጎት ማሳየቱ የሚበረታታ ነው ያሉት አምባሳደሩ ይህ የዩኒቨርሲቲው ፍላጎት ዕውን እንዲሆን በዩኒቨርሲቲው የሚሠሩ የሕንድ መምህራን ጉልህ ሚና እንዲጫወቱ ኤምባሲያቸው አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ጠቁመዋል፡፡

የምርምር ዳይሬክቶሬት ኤክስኪዩቲቭ ዳይሬክተር ዶ/ር ተስፋዬ ሀብተማርያም በዩኒቨርሲቲው አሁን ላይ ከተለያዩ የሀገር ውስጥና የውጭ ተቋማት ጋር ዘርፈ ብዙ የትብብር ፕሮጀክቶች እየተከናወኑ መሆናቸውን ተናግረው በዋናነት ዩኒቨርሲቲው ቤልጂየም፣ ኔዘርላንድ፣ ሲውዘርላንድ፣ እንግሊዝ፣ ኢንዶኔዥያ፣ ሕንድ፣ ጀርመንና ሌሎች ሀገራት ጋር ከሚገኙ የተለያዩ ተቋማት ጋር በትብብር እየሠራ ነው ብለዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው በግብርና፣ ጤና፣ በሐሩራማ አካባቢዎች በሽታዎች፣ በቱሪዝም፣ በአንትሮፖሎጂ፣ በአርኪዮሎጂ፣ በማዕድን ልማትና ሌሎች መስኮች ከተለያዩ ተቋማት ጋር በትብብር ለመሥራት ዝግጁ መሆኑንና ለነዚህም ሥራዎች መሳካት ዩኒቨርሲቲው አስቻይ ሁኔታዎችን የሚፈጥሩ አዳዲስ አሠራሮች መዘርጋቱን ጠቁመዋል፡፡ በአሁኑ ሰዓት በዩኒቨርሲቲው 127 የውጭ ሀገር መምህራን ይገኛሉ ያሉት ዶ/ር ተስፋዬ እነዚሁ መምህራን የዩኒቨርሲቲውን የሥራ አቅጣጫ በመገንዘብ በሀገራቸው ከሚገኙ የተለያዩ ተቋማት ጋር በትብብር ለመሥራት የሚያስችሉ ግንኙነቶችን ለመፍጠርና በተግባር ለማዋል በትኩረት ሊሠሩ ይገባል ብለዋል፡፡

በመርሃ ግብሩ በሕንዳውያን መምህራን የተዘጋጁ 5 የትብብር ሥራ ንድፈ ሃሳቦች የቀረቡ ሲሆን “Establishment of Common Incubator and Training Facility for Diary and Fruits Processing” በሚል ርዕስ በDr. S. Babuskin የቀረበው ይገኝበታል፡፡ በኢትዮጵያ ከ5 ሚሊየን በላይ ሕዝብ የኑሮ መሠረቱ በአትክልትና ፍራፍሬ ማምረት ላይ እንደሆነ ጠቁመው በዚህም የማምረት ሂደት ውስጥ ከ30 እስከ 40 ከመቶ የሚሆነው ምርት በተለያዩ ምክንያቶች እንደሚባክን ጠቁመዋል፡፡ ሕንድ ሀገር ከሚገኙ ተቋማት ጋር ትብብር በመፍጠር የወተትና የፍራፍሬ ማቀነባበሪያ ማዕከላትን ማቋቋም፣ አምራቾችን ማሠልጠንና እሴት የተጨመረባቸው ምርቶችን እንዲያመርቱ ማስቻል እና የምርት ብክነትን መቀነስ የፕሮጀክታቸው ትኩረት መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት