Print

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ከኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አስተዳደር /INSA/ ጋር በመተባበር በድሮን ካሜራ አጠቃቀም ዙሪያ ከዩኒቨርሲቲው የተለያዩ የትምህርትና ሥራ ክፍሎች ለተወጣጡ መምህራን፣ ተመራማሪዎችና ባለሙያዎች እንዲሁም ከነጭ ሳር ብሔራዊ ፓርክና ከ“GIZ” ለተወጣጡ ባለሙያዎች ከሚያዝያ 3-12/2014 ዓ/ም ድረስ ለ10 ቀናት የቆየ ሥልጠና ሰጥቷል፡፡ 

ሥልጠናው ከኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አስተዳደር /INSA/ በመጡ 4 የመስኩ ባለሙያዎች በክፍል ውስጥ በጽንሰ ሃሳብ እንዲሁም በተዘጋጁ 3 ድሮኖች አማካኝነት በተግባር ተደግፎ መስክ ላይ የተሰጠ ነው፡፡  ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ 

የዩኒቨርሲቲው ምርምርና ማኅበረሰብ አገ/ት ም/ፕሬዝደንት ተ/ፕ በኃይሉ መርደኪዮስ የድሮን ቴክኖሎጂ በአሁኑ ሰዓት በዓለማችን ለተለያዩ ዓላማዎች በስፋት አገልግሎት ላይ እየዋለ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡ ቴክኖሎጂው እንደ ዩኒቨርሲቲ ከተፈጥሮ ሀብት መራቆት፣ ከደን መልሶ ማልማትና ከማዕድን ሀብቶች መጠንን ከማወቅ አንፃር ለሚከናወኑ የምርምር ሥራዎች በእጅጉ አጋዥ እንደሚሆን ም/ፕሬዝደንቱ ጠቅሰዋል፡፡ ከዚህም ባሻገር ቴክኖሎጂው በዞን፣ በከተማና በዩኒቨርሲቲ ደረጃ የሚከወኑ ሁነቶችን፣ የምርምር ውጤቶችን፣ የሥራ እንቅስቃሴዎችን፣ የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ሀብቶችን ማራኪ በሆነ መልኩ ተደራሽ ከማድረግ አንፃር ቴክኖሎጂው የጎላ ሚና የሚጫወት ነው ያሉት ም/ፕሬዝደንቱ ሠልጣኞች ከሥልጠናው ያገኙትን ዕውቀት በተግባር ማዋል ይጠበቅባቸዋል ብለዋል፡፡   

የማኅበራዊ ሳይንስና ስነ-ሰብ ኮሌጅ ዲንና የሥልጠናው አስተባባሪ ዶ/ር ሙሉጌታ ደበሌ በበኩላቸው ሥልጠናው ቴክኖሎጂውን በይበልጥ ይጠቀሙበታል ተብለው ከታሰቡ የዩኒቨርሲቲው ባዮሎጂ፣ ጂኦሎጂ፣ ጂኦግራፊ፣ ሶሾሎጂ፣ ጤና ኢንፎርማቲክስ፣ ተፈጥሮ ሀብት አጠባበቅ፣ ከተማና መሬት ፕላን ትምህርት ክፍሎች ለተወጣጡ መምህራን፣ ተመራማሪዎች፣ ለዩኒቨርሲቲው ኮሚዩኒኬሽን ዘርፍ የካሜራ ባለሙያዎች፣ ከ“IUC” ፕሮግራም፣ ከነጭ ሳር ብሔራዊ ፓርክና ከ“GIZ” ለተወጣጡ ሙያተኞች የተሰጠ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ በድሮን ካሜራ ቴክኖሎጂ ጽንሰ ሃሳብና አጠቃቀም ዙሪያ በተግባር የተደገፈ በቂ ግንዛቤ በመፍጠር በዩኒቨርሲቲው የሚገኙ ድሮን ካሜራዎችን ለምርምርና ለሌሎች የኮሚዩኒኬሽንና የገጽታ ግንባታ ሥራዎች በአግባቡ እንዲውሉ ማስቻል የሥልጠናው ዋነኛ ዓለማ መሆኑንም ዶ/ር ሙሉጌታ ጠቁመዋል፡፡

በኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አስተዳደር /INSA/ በኤሮስፔስ ዲቪዥን ውስጥ የድሮን ኦፕሬሽን ቡድን የድሮን ቴክኒሻን የሆኑት አሠልጣኝ አቤል ለገሠ በድሮን ካሜራ ቴክኖሎጂ ምንንት፣ የአጠቃቀም መመሪያዎችና መርሆች፣ የድሮን ካልብሬሽን አሠራር፣ የመረጃ አያያዝ፣ የተለያዩ መተግበሪያዎች አጠቃቀም፣ ድሮን ካሜራ የማብረር ቴክኒኮችና ጥንቃቄዎች በሚሉ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ሥልጠናው ትኩረት ማድረጉን ተናግረዋል፡፡ የድሮን ቴክኖሎጂ ለተለያዩ ተግባራት ሊውል የሚችል መሆኑን የተናገሩት አሠልጣኙ ሠልጣኞች ከሥልጠናው ያገኙትን የጽንሰ ሃሳብና የተግባር ግንዛቤ በመጠቀም ቴክኖሎጂውን እንደ ዩኒቨርሲቲ አስፈላጊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ሊጠቀሟቸው ይገባል ብለዋል፡፡

ከሠልጣኞች መካከል ከነጭ ሳር ብሔራዊ ፓርክ የመጡት የዱር እንስሳት ቱሪዝም ባለሙያው አቶ ተካ ደርበው በሥልጠናው የድሮን ቴክኖሎጂን መጠቀም የሚያስችል በተግባር የተደገፈ ዕውቀት ማግኘታቸውን ገልጸው ቴክኖሎጂው ፓርኩን ከማስተዳደርና በፓርኩ ውስጥ የሚገኘውን ብዘሃ ሕይወት ከመቆጣጠር አንፃር የጎላ ፋይዳ ይኖረዋል ብለዋል፡፡ አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በሥልጠናው እንዲሳተፉ ስለጋበዛቸው በፓርኩ አስተዳደር ስም ምሥጋናቸውን አቅርበዋል፡፡

በዩኒቨርሲቲው የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት የካሜራ ባለሙያ የሆኑት አቶ ፍስኃ ገ/ሥላሴ በበኩላቸው ሥልጠናው ከወቅቱ ጋር አብሮ የሚሄድና አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን እንድንጠቀም የሚረዳ ነው ብለዋል፡፡ የድሮን ቴክኖሎጂ ከኮሚዩኒኬሽን ሥራዎች ባሻገር ለሌሎች የዩኒቨርሲቲው የሥራ ክፍሎችም ብዙ ጠቀሜታ ያለው መሆኑን በሥልጠናው መገንዘባቸውን የገለጹት አቶ ፍሰኃ እንደ ኮሚዩኒኬሽን የሥራ ክፍል ቴክኖሎጂውን በአግባቡ መጠቀም ከተቻለ የሕዝብ ግንኙነት ሥራውን አንድ እርምጃ ከፍ ያደርጋል ብለው እንደሚያምኑ ተናግረዋል፡፡

በዩኒቨርሲቲው ማኅበራዊና ስነ-ሰብ ኮሌጅ የሶሾሎጂና ሶሻል አንትሮፖሎጂ መ/ርት ሜሮን አህመድ በበኩላቸው በሥልጠናው በቆዩባቸው 10 ቀናት ከቴክኖሎጂው ጋር የተያያዙ በርካታ አዳዲስ ዕውቀቶችን ማግኘታቸውን ተናግረው ቴክኖሎጂው በሶሾሎጂና ሶሻል አንትሮፖሎጂ መስክ የሚከናወኑ ምርምሮችን ከማገዝ አንፃር ጉልህ ሚና እንደሚጫወት ጠቁመዋል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት