Print

‹‹Open Forum on Agricultural Bio-technology›› በሚል ርዕስ ‹OFAB-Ethiopia› የደቡብ ምዕራብ ቅርንጫፍ ያዘጋጀው ፎረም ሚያዝያ 08/2014 ዓ/ም በዩኒቨርሲቲው የተፈጥሮና ቀመር ሳይንስ ኮሌጅ ባለ ድርሻ አካላት በተገኙበት ተካሂዷል፡፡

የግብርና ባዮ-ቴክኖሎጂ በማኅበረሰቡ ዘንድ ያለውን ተቀባይነት ለመገምገምና በቀጣይ ድርጅቱ ከባለ ድርሻ አካላት ጋር ትስስር በመፍጠር የጀመራቸውን የተለያዩ ተግባራት አጠናክሮ ለመቀጠል በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ የጋራ መግባባት ለመፍጠር ፎረሙ መዘጋጀቱ ተገልጿል፡፡ ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

በፎረሙ OFAB በአፍሪካና በኢትዮጵያ የተቋቋመበት ዓላማ፣ ድርጅቱ ኢትዮጵያ ውስጥ ባሉ የተለያዩ የመንግሥትና የግል ተቋማት፣ በዩኒቨርሲቲዎችና በሌሎች በደቡብ ምዕራብ ቅርንጫፍ እያከናወነ ያለው ተግባር፣ የግብርና ባዮ-ቴክኖሎጂን መጠቀም በተለይ ለሰብልና ለእንስሳት ምርምር ውጤታማነት ያለው አስተዋጽኦ፣ ዘረመላቸው የተለወጡ የሰብል ዝርያዎች በኢትየጵያና በዓለም አቀፍ ደረጃ ያሉበትን ሁኔታና እያበረከቱ ያለው አስተዋጽኦ፣ ድርቅን መቋቋም የሚችሉ የበቆሎ ዝርያዎች ላይ እየተደረጉ ያሉ ምርምሮች፣ አዲሱን ቴክኖሎጂ በመጠቀም አሲዳማነትን መቋቋም የሚችሉ የገብስ ዝርያዎችን ውጤታማ ማድረግ የሚሉና ሌሎች ከባዮ-ቴክኖሎጂ ጋር ተዛማጅ ጉዳዮች ተነስተዋል፡፡

የምርምርና ማኅበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዝደንት ተ/ፕ በኃይሉ መርደኪዮስ እንደገለጹት የሚመለከታቸው ባለ ድርሻ አካላት በፎረሙ መገኘታቸው በተለይ በሀገሪቱ የተከሰተውን ወቅታዊ የገበያ ጫና በማረጋጋት የተሻለ አቅርቦት እንዲፈጠር በምርምር የተገኙ ውጤቶችን ወደ ታች ለማውረድና የሀገሪቱን የልማት ዕቅድ ለማሳካት ፋይዳው የጎላ ነው፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ እንደ ምርምር ዩኒቨርሲቲ OFAB ለሚያከናውናቸው ምርምሮችና ማኅበረሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ የሚሠራቸውን ሥራዎች ለመደገፍ በተለይ ከትምህርትና ከምርምር ከተቋማት፣ ከአምራች ማኅበራት፣ ከሚመለከታቸው ክፍሎችና ሌሎች ባለ ድርሻ አካላት ጋር በትብብርና በቅንጅት ከመሥራት ባለፈ አፈጻጸማቸውን ከግብ ለማድረስ የበኩሉን እንደሚያደርግ ም/ፕሬዝደንቱ ተናግረዋል፡፡ እንደ ተ/ፕ በኃይሉ ባዮ-ቴክኖሎጂ በሀገር አቀፍ ደረጃ ትኩረት ተሰጥቶት እንደ አንድ የትምህርት ዘርፍ እንዲታቀፍ የተደረገ ሲሆን በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲም በመጀመሪያና በ2ኛ ዲግሪ መርሃ ግብሮች እየተሰጠ ይገኛል፡፡

የOFAB-Ethiopia የደቡብ ምዕራብ ቅርንጫፍ አስተባባሪ ዶ/ር ዓለማየሁ ኃ/ሚካኤል እንደተናገሩት ድርጅቱ ከ2009 ዓ/ም ጀምሮ ከኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ጋር የመግባቢያ ውል ስምምነት ተፈራርሞ ኢትዮጵያ ውስጥ ባሉት ቅርንጫፎች የምግብ ዋስትና፣ የአየር ንብረት ለውጥ፣ የግብርና ልማትና የአካባቢ ጥበቃ ላይ ምርምሮችን የሚያደርግ ሲሆን በተለያዩ ዘርፎች የሠለጠኑ ምሁራን እንዲወጡ፣ ከሚመለከታቸው ክፍሎች ጋር የሚያገናኙ አካላት እንዲፈጠሩና በማስረጃ የተደገፉ ዓለም አቀፍ ጉዳዮች ላይ የሚንቀሳቀሱ ውሳኔ ሰጪዎች እንዲኖሩ እየሠራ ይገኛል፡፡

እንደ አስተባባሪው ገለጻ ከባለ ድርሻ አካላት ጋር ትስስር መፈጠሩ በግብርና ባዮ-ቴክኖሎጂ ዘርፍ ለሚንቀሳቀሱ አካላት የመረጃ እጥረት እንዳያጋጥም፣ ሀሰተኛና ያልተረጋገጡ መረጃዎችን ለመከላከል እንዲሁም ምርታማ፣ በሽታና የአየር ንብረት

መዛባት የሚያስከትለውን ጫና መቋቋም የሚችሉ ሰብሎች ላይ በስፋት ምርምሮችን ለማካሄድ ይረዳል፡፡ ፎረሙ ተሳታፊዎቹ በቀጣይ ለሚሠሩ ሥራዎች ራሳቸውን እንዲያዘጋጁ፣ አቅማቸውን አውጥተው እንዲጠቀሙ እንዲሁም ባለ ድርሻ አካላት በኃላፊነት እንዲሠሩ መሠረት የሚጥል መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

የOFAB-Ethiopia ሴክሬታሪያት ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክተርና የፕሮግራሙ መሪ መ/ር ደረሰ ተሾመ ፎረሙ የማኅበረሰቡን ሕይወትና ሀገሪቱ ያለችበትን ሁኔታ ለማስተካከል በምርምር የሚሳተፉ የመንግሥትና የግል ተቋማትን በዓለም አቀፍ ደረጃ በየአካባቢው በቅርንጫፍ (Node) ደረጃ በማዋቀር በተለይ በግብርና ባዮ-ቴክኖሎጂ ዘርፍ የዕውቀትና የልምድ ልውውጥ እንዲኖር ያግዛል ብለዋል፡፡

የOFAB-Ethiopia ግብርና ኤክስቴንሽን ኢንስቲትዩት ከፍተኛ ተመራማሪ ዶ/ር ታደሰ ዳባ ባዮ-ቴክኖሎጂ ኢትዮጵያን በመሳሰሉ በማደግ ላይ ያሉ ሀገራት ጤናን፣ ግብርናን፣ የአካባቢ ጥበቃንና ሌሎች መሠረታዊ ዘርፎችን ሳይንሳዊ በሆነ መልኩ ለመደገፍ ሥራ ላይ የዋለ አዲስ የምርምር ቴክኖሎጂ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

እንደ ዶ/ር ታደሰ ከዚህ ቀደም በግብርናው ዘርፍ የማይቻሉና አስቸጋሪ የነበሩት በአዲሱ የግብርና ባዮ-ቴክኖሎጂ የተሻሉ ውጤቶች እያስመዘገቡ የመጡ ሲሆን በተለይ በባለሙያዎች ብዙ ጥያቄ ሲያስነሱ የነበሩ ዘረመላቸው የተቀየሩ ሰብሎች ጥቅምና ጉዳት፣ የግብርና ባዮ-ቴክኖሎጂ ለሀገራችን የሚኖረው ጠቀሜታና መሟላት የሚገባቸው ሁኔታዎች ላይ ከሚመለከታቸው ባለ ድርሻ አካላት ጋር በመወያየት መፍትሄ ለመስጠትና ግንዛቤን ለመፍጠር ፎረሙ አስተዋጽኦ አለው፡፡

OFAB ከኢትዮጵያ በተጨማሪ በጋና፣ ናይጄሪያና በተወሰኑ የአፍሪካ ሀገራት መሰል እንቅስቃሴዎችን እያካሄደ ይገኛል፡፡ በፎረሙ ከ8 ዩኒቨርሲቲዎች፣ ከ6 የእርሻ ምርምር ተቋማትና ማዕከላት፣ ከ4 የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች የመጡ አመራሮች እንዲሁም በግብርና ዘርፍ ሥራ ፈጠራ ላይ የተሰማሩ የግልና የመንግሥት ባለ ድርሻ አካላት፣ የባዮ-ቴክኖሎጂና የእርሻ ምርምር ከፍተኛ ተመራማሪዎችና ባለሙያዎች ታድመዋል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት