በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ለሕክምና ት/ቤት መመህራንና ተማሪዎች አገልግሎት የሚውል “UpToDate” የተሰኘ ሶፍትዌርን ለ5 ዓመታት በነፃ የመጠቀም ፈቃድ ማግኘቱ ተገለፀ፡፡

የሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ቺፍ ኤክስኪዩቲቭ ዳይሬክተር ዶ/ር ታምሩ ሽብሩ “UpToDate” በመባል የሚታወቀው ሶፍትዌር በዓለማችን በርካታ ሐኪሞች በፀሐፊነትና በገምጋሚነት የሚሳተፉበት ሐኪሞች በማስረጃ ላይ የተመሠረተ ክሊኒካል ውሳኔ እንዲሰጡ ለማስቻል እንደ ዋቢ የሚያገለግል ለሕክምናው ዘርፍ በእጅጉ ጠቃሚ የሆነ ሶፍትዌር መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ይህንን ሶፍትዌር በሕጋዊ መንገድ ለመጠቀም ክፍያ የሚያስፈልግ መሆኑን የገለጹት ዶ/ር ታምሩ ከሶፍትዌሩ አምራች ኩባንያ ጋር በተፈጠረ ግንኙነት ሶፍትዌሩን በነፃ ለ5 ዓመታት የመጠቀም ዕድል ማግኘት መቻሉን ተናግረዋል፡፡ የተገኘው ዕድል በኮሌጁ ሕክምና ት/ቤት ላሉ መምህራንና ተማሪዎች ትልቅ ዕድል በመሆኑ በስልካቸውና በግል ኮምፕዩተሮቻቸው ሶፍትዌሩን በመጫንና በመዘገብ የተገኘውን ዕድል በአግባቡ እንዲጠቀሙ አሳስበዋል፡፡

“UpToDate” በመባል የሚታወቀው ሶፍትዌር አሜሪካ ሀገር የሚገኝ “Wolters Kluwer” የተሰኘ ኩባንያ ምርት ሲሆን ከ12 ሺህ በላይ ክሊኒካዊ ርዕሶችን በ25 ስፔሻሊቲዎች ጋር የያዘ፣ ከ9,500 በላይ ደረጃ የተሰጣቸው (Graded) ምክረ ሃሳቦች የተካተቱበት፣ ከ6,900 በላይ ልዩ የመድኃኒት ማውጫ (Entries) ያሉበትና ከ200 በላይ የሕክምና ካልኩሌተሮችን ያካተተ ሶፍትዌር መሆኑን ማወቅ ተችሏል፡፡

http://www.uptodate.com/online

 

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት