Print

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንት ጽ/ቤት በከፍተኛ ትምህርት አመራር መረጃ ሥርዓት /Higher Education Management Information System (HEMIS)/ዙሪያ ለዩኒቨርሲቲው ካውንስል አባላት ሚያዝያ 11/2014 ዓ/ም ገለጻ ሰጥቷል፡፡ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ የተለያዩ ውሳኔዎች የሚተላለፉትና በርካታ ሥራዎች የሚከናወኑት መረጃን መሠረት አድርገው በመሆኑ መረጃ ለአንድ ሥራ ውጤታማነት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው ተናግረዋል፡፡ ይሁን እንጂ እንደ ሀገርም ሆነ እንደ ተቋም የመረጃ አያያዝና አጠቃቀማችን ክፍተቶች የሚስተዋሉበት ነው ያሉት ፕሬዝደንቱ HEMIS ይህንን ክፍተት ለማስተካከል የሚረዳ ቴክኖሎጂ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ የመረጃ ሥርዓቱ ተማሪዎችንና ሠራተኞችን እንዲሁም መሠረተ ልማትን የተመለከቱ መረጃዎች ግልፅ ሆነው ተቀምጠው በየደረጃው ያሉ አካላት እንዲጠቀሙበትና በዚያው ልክ እንዲሠሩ ምቹ ሁኔታን የሚፈጥር መሆኑን ፕሬዝደንቱ ተናግረዋል፡፡

እንደ ፕሬዝደንቱ የገለጻው ዋና ዓላማ ተሳታፊዎቹ የዩኒቨርሲቲው የካውንስል አባላት እንደመሆናቸው በቀጣይ ለሚሠሩ መረጃን የማደራጀት ሥራዎች በባለቤትነት ስሜት ኃላፊነት ወስደው አንዲሠሩ ማድረግ ነው፡፡ በመረጃ አሰባሰብ ሂደት ክፍተት እንዳይፈጠር ከስትራቴጂክ ዕቅድ ዝግጅት፣ ክንውንና ግምገማ እና ከመረጃና መገናኛ ቴክኖሎጂ ዳይሬክቶሬቶች የተወጣጡ ባለሙያዎች በየሥራና በየትምህርት ክፍሉ በመገኘት ድጋፍ ያደርጋሉ ብለዋል፡፡ መረጃ ተለዋዋጭ በመሆኑ ከማዕከል ወይም ከሌላ አካል መረጃ ሲፈለግ ብቻ ሳይሆን እንደ ዩኒቨርሲቲ በየሦስት ወሩ መታደስ ያለበት በመሆኑ የተቋሙን ሠራተኛና ተማሪ ትክክለኛና ወቅታዊ መረጃ ለመያዝ ሁሉም የሥራ ክፍል ኃላፊዎች በትኩረት መሥራት እንዳለባቸው ፕሬዝደንቱ አሳስበዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ስትራቴጂክ ዕቅድ ዝ/ክ/ግ/ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ አስፋው ደምሴ በበኩላቸው HEMIS በሀገር አቀፍ ደረጃ በዩኒቨርሲቲዎች እና ቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች ላይ የሚታየውን የመረጃ አያያዝ ክፍተት ለመቅረፍ የተፈጠረ ሶፍትዌር መሆኑን ገልጸው ሶፍትዌሩ መረጃን አስተማማኝ በሆነና በተሻለ መልኩ ማቆየት እንዲችል ተደርጎ የተሠራ ነው ብለዋል፡፡ እንደ ዳይሬክተሩ በዩኒቨርሲቲ ደረጃ ከየሥራ ክፍሉ የተሰበሰቡ መረጃዎች ለፕሬዝደንት ቀርበው ሲረጋገጡ ለትምህርት ሚኒስቴር የሚተላለፍ ይሆናል፡፡ ከዚህ ቀደም በዩኒቨርሲቲው የተለያዩ ሶፍትዌሮች አገልግሎት እየሰጡ ቢሆንም ይህ ሶፍትዌር ዩኒቨርሲቲዎች በሰው ኃይል፣ በገንዘብና በበጀትም ጭምር ያላቸውን መረጃ በአንድ ላይ አጠቃሎ መዝግቦ የሚይዝ የተሻሻለ ግኝት እንደሆነ ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል፡፡

የስትራቴጂክ ዕቅድ ዝ/ክ/ግ/ ዳይሬክቶሬት ቡድን መሪ አቶ ሰሎሞን ይፍሩ HEMIS የመረጃ አያያዝና ልውውጥ ሥርዓቱን ዘመናዊና የተቀላጠፈ ማድረግ የሚያስችል በትምህርት ሚኒስቴር የተሠራ የሙከራ ሶፍትዌር መሆኑን ገልጸው ከሙከራው በኋላ ሙሉ በሙሉ ወደ ትግበራ ይገባል ብለዋል፡፡ እንደ አቶ ሰሎሞን ሶፍትዌሩ በኢትዮጵያ ያሉ የግልና የመንግሥት ትምህርት ተቋማትን መረጃ አንድ ላይ ሰብስቦ ወደ አንድ የመረጃ ቋት የማስገባት ዓላማን ያነገበ ሲሆን ከዚህ በፊት በሰውና በወረቀት ላይ ብቻ ያተኮረ የአሠራር ዘዴን እንደ ከፍተኛ የትምህርት ተቋም ወደ ዘመናዊ አሠራር የሚቀይር መሆኑን ተናግረዋል፡፡

መረጃን በአንድ ቋት መያዝ ዘርፈ ብዙ ጥቅም እንዳለው የገለጹት ቡድን መሪው በቅርቡ በሀገራችን በተከሰተው የሰሜኑ ክፍል ጦርነት በአካባቢው ያሉ ተማሪዎች መረጃ በዩኒቨርሲቲ ደረጃ ብቻ በመኖሩ ተማሪዎቹ ቀሪ መረጃ ለማግኘት መቸገራቸውን ተናግረዋል፡፡ ሶፍትዌሩ መረጃን በአንድ ማዕከል አደራጅቶ በመያዝ መረጃው ከተቋሙ ቢጠፋ እንኳን ማዕከል ላይ ቀሪ እንዲኖር የሚያስችል ቴክኖሎጂ በመሆኑ መሰል ችግሮችን ለመቅረፍ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንደሚኖረው ጠቁመዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ለመንግሥት በጀት አመዳደብ፣ ለፖሊሲ አውጪ አካላት፣ ለግልፀኝነትና ለመሳሰሉ ተግባራት የሚያመች ሲሆን ተቋማት ደረጃውን የጠበቀና ወጥ የመረጃ አያያዝ ሥርዓት እንዲኖራቸው ያስችላልም ብለዋል፡፡

በገለፃው የዩኒቨርሲቲው ካውንስል አባላትና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት የተሳተፉ ሲሆን በወቅቱ ለተነሱ የተለያዩ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት