Print

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የሥራ ፈጠራ ልማትና ማበልጸጊያ ማዕከል በላንቴ ቀበሌ በማኅበር ተደራጅተው ለሚሠሩ፣ የግል ሥራ ፈጥረው ለሚንቀሳቀሱና ሥራ አጥ ለሆኑ ወጣቶች በመሠረታዊ የሥራ ፈጠራ አመለካከትና ክሂሎት ዙሪያ ሚያዝያ 10/2014 ዓ/ም ሥልጠና ሰጥቷል፡፡

ጽኑ ጉጉት፣ ተነሳሽነት፣ ውድቀት፣ ጽናት ማጣት፣ ሥራን ለመፍጠር ምቹ አጋጣሚን መፈለግና ለስኬት የሚያበቁ ግላዊ የሥራ ፈጠራ ብቃት መመዘኛዎች ሥልጠናው ያተኮረባቸው ነጥቦች ናቸው፡፡ ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የሥራ ፈጠራ ልማትና ማበልጸጊያ ማዕከል ዳይሬክተር ዶ/ር ወንድወሰን ጀረኔ ዩኒቨርሲቲው ከመማር ማስተማር ሥራ በተጨማሪ ለምርምርና ለማኅበረሰብ አገልግሎት ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ እንደሚገኝ ጠቁመው ሥልጠናው ወጣቶች ያገኙትን ዕውቀትና ክሂሎት ለሌሎች በማካፈል በቀጣይ የሚጀምሩትን ሥራ ማሳደግና ውጤታማ መሆን እንዲችሉ በእጅጉ ያግዛል ብለዋል፡፡

የሥራ ፈጠራ ልማትና ማበልጸጊያ ማዕከል አስተባባሪ መምህር አበበ ዘየደ ሠልጣኞች የራሳቸውን ክፍተት ተረድተው በአካባቢያቸው የሚገኙ ነገሮችን በመጠቀም ተሰጥኦቸውን ወደ ገንዘብ መቀየር እንዲችሉ የአመለካከት ለውጥ ለመፍጠር ሥልጠናው መዘጋጀቱን ገልጸዋል፡፡

አስተባባሪው ከዚህ ቀደም ሥልጠናው ለአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ብቻ ይሰጥ እንደነበር አስታውሰው መሰል ሥልጠናዎችን ወደ ማኅበረሰቡ ማውረድ ሥራ ፈጣሪና የተነቃቃ ማኅበረሰብ ለመፍጠር የጎላ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ብለዋል፡፡ ወጣቶቹ በአካባቢያቸው ያሉትን የተፈጥሮ ጸጋዎች ተጠቅመው ሥራ ፈጣሪ እንዲሆኑ ለማበረታታት እንዲሁም በቀበሌው ያሉ ማኅበራት አቅማቸውን አሳድገው በሀገር አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ መሆን እንዲችሉ ተነሳሽነትን ለመፍጠር ሥልጠናው እንደሚረዳም ተናግረዋል፡፡

ሥልጠናው በቀጣይ ከላንቴ በተጨማሪ በሸሌ፣ ሻራና አርባ ምንጭ ከተማን ጨምሮ በሌሎች ወረዳዎችም እንደሚሰጥ ተገልጿል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት